19/09/2026
የህዝቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ፣ የአርሶአደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የመስኖ ልማትን ባህል ለማድረግ በቁርጠኝነት ይሰራል፦ ኢንጂነር በዛብህ ገበየሁ
ላስካ፡ መስከረም 9/2019 ዓ.ም(ላስካ ኮሙኒኬሽን)
የባስኬቶ ዞን ግብርና መምሪያ ለኢልኒኖ ክስተት የማይበገር ግብርናን መገንባት በሚል መሪ ዞናዊ የንቅናቄ መድረክ አካሄደ።
በዝናብ ብቻ የተመሰረተ ግብርናን በመቀነስ መስኖን ወደ ዋና የግብርና ልማት አማራጭ በማምጣት የህዝቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና የአርሶአደሩን ምርታማነት በማሳደግ፤ በአየር ንብረት መዛባት የሚመጡ ስጋቶችን ለመቀነስ በትኩረት ልሰራ እንደሚገባ የባስኬቶ ዞን አስተዳዳሪ ኢንጂነር በዛብህ ገበየሁ አስገንዝበዋል።
ኤልኒኖ ክስተት የማይበገር ግብርና ለመገንባት ለመስኖ ተስማሚ የሆኑ መሬቶችን ማልማት፣ የውሃ ሀብቶችን በአግባቡ መጠቀም፣ ድርቅን የሚቋቋሙ ሰብሎችን ማስፋፋት፣ የግብርና ግብዓትና የኤክስቴንሽን አገልግሎትን ማጠናከር እንዲሁም ወጣቶችና ሴቶችን በመስኖ ልማት ማሳተፍ እንደሚገባ ኢ/ር በዛብህ ተናግረዋል።
በግብርና ዘርፍ የተገኙ ስኬቶች የአርሶ አደሩ ትጋትና የመንግሥት ትኩረት ፍሬ መሆናቸውን የገለፁት አስተዳዳሪው አስፍቶ በማቀድ፣ ቴክኖሎጂ በመጠቀምና የህዝብ ተሳትፎ በማጣመር ፈተናዎችን ወደ ዕድል መቀየር እንደሚቻል ተናግረዋል።
ኤልኒኖን በመቋቋም ዘመናዊና የማይበገር ግብርና ለመገንባት በቅንጅት መስራት ይገባል ያሉት የባስኬቶ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተመስገን አዘነ የኤልኒኖ ተጽዕኖን በመቋቋም የኢኮኖሚ አቅምንና የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ እንደሚሰራ አክለዋል።
በአጭር ጊዜ የሚደርሱና ድርቅን የሚቋቋሙ ሰብሎችን በማልማት፣ የሰብል ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ እርጥበትን የሚይዙ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራዎችን በማጠናከር፣ የተገነቡ የመስኖ ተቋማትንና ሌሎች የውሃ አማራጮችን በአግባቡ በመጠቀም የሰብልና የእንስሳት ምርትን ለማሳደግ በብቃትና በቁርጠኝነት ባለድርሻ አካላት እንዲሰሩ አቶ ተመስገን አሳስበዋል።
የኤልኒኖን ተጽእኖ ለመቀልበስ እና የተሻሻለ የእንስሳት ዲቀላ አገልግሎት ዙሪያ የተዘጋጀ ሰነድ በባለድርሻ አካላት የቀረበ ሲሆን በቀረበው ስነድ ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።
የመስኖ መሬትና የውሃ ሀብት ልማት በተገቢው በመጠቀም አርሶ አደር ከልማቱ ውጭ እንዳይሆን በተግባር እንደሚሰራ በመድረኩ ተመልክቷል።
“ከተረጂነት ወደ ምርታማነት” ለመሸጋገር የተጀመሩ የግብርና ኢኒሼቲቮችን በቁርጠኝነት በመፈጸም የሀገር የኢኮኖሚ አቅምን ማጠናከር እንደሚገባ ተገልጿል።
በመጨረሻ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ሽግግርን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመሸፈን ሥራዎችን በመስክ ምልከታ አድርገዋል።
መስከረም 9/2019 ዓ.ም
ላስካ