02/06/2026
ህዝባችን በምርጫው ያሳየዉን ቆራጥነት በዞኑ በተጀመሩ በሌሎች የልማት ዘርፎች ላይ ሊደግም ይገባል - ክቡር አቶ ሙህዲን ሁሴን
===========
ግንቦት 25/2018
የሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ሙህዲን ሁሴን በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሀላባ ዞን ባሉ የተለያዩ ምርጫ ክልሎች የተደረገው የምርጫ ሂደት ከድምጽ አሰጣጥ ጀምሮ እስከ ድህረ ምርጫ ድረስ በሰላም፣ በቅንጅት እና በትብብር በመጠናቀቁ ለመላው ለዞኑ ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዚህም የሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ሙህዲን ሁሴን እንደገለጹት የዞናችን ህዝብ በምርጫው ያሳዩትን ቆራጥነት በተጀመሩ በሌሎች የልማት ዘርፎች ሊደግሙት እንደሚገባ ገለጹ።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ የዞኑ ህዝብ በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላሳየው ትዕግስትና ቆራጥነት ምስጋና አቅርበዋል።
በዞኑ በሚገኙ የተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ህዝቡ ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል፣ ዝናብና ፀሐይ ሳይበግራቸው ድምጻቸውን ሰጥተዋል ብለዋል።
የዞናችን ህዝብ ሁልጊዜም ለሀገራዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ያላቸውን ቀዳሚና የነቃ ተሳትፎ በከፍተኛ አክብሮት ማድነቃቸውን ተናግረዋል።
ለሀላባ ዞን ህዝብና ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ዛሬ በዞናችንም ሆነ በሀገራችን ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የተጻፈበት ታላቅ ቀን መሆኑን ገልጸዋል።
ዜጎች ሉዓላዊ ስልጣናቸውን በምርጫ ካርዳቸው አማካኝነት በነፃነት የሚገልጹበት 7ኛው ሀገራዊ እና ክልላዊ ምርጫ በሀላባ ዞን በሁሉም የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ፍጹም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃ እና ስኬታማ በሆነ መልኩ ተጠናቀዋል ብለዋል።
ይህም የምርጫ ሂደት ማህበረሰባችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማስቀጠል ያለውን የበሰለ የፖለቲካ ባህል እና ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበት መሆኑን ተናግረዋል።
በሂደቱም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ላሳዩት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፉክክር፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ታዛቢዎችና ወኪሎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካለት ላሳያችሁት የሀገርና የህዝብ ውግንና በዞኑ አስተዳደርና በሀላባ ህዝብ ምስጋና መቅረባቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ የተካሄደው የምርጫ ሂደት ያለምንም የጸጥታ ስጋት ሙሉ በሙሉ ሰላማዊና ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ታላቅ ሀላፊነት ለተወጡ የጸጥታ አካላት፣ ለመላው የዞኑ ማህበረሰብ፣ እና ሌሎች ለሚመለከታቸው ባለድርሻ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በተለይም ሚዲያዎች በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት የምርጫ ሂደቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ወቅታዊና ፈጣን መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማድረሳቸው ምስጋና መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከምርጫው ማግስትም መላው የዞናችን ነዋሪዎች የተለመደውን አንድነት፣ አብሮነት እና ወንድማማችነት ይበልጥ በማጠናከር፣ ፊታችንን ሙሉ በሙሉ ወደ ልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች በማዞር የጋራ ብልጽግናችንን ለማረጋገጥ በጋራ መቆም እንደሚገባ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በመጨረሻም፣ በአሁኑ ወቅት በየምርጫ ጣቢያው የተለጠፉ ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቶችን በትዕግስት በመመልከት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋዊ ውጤት እስኪሰጥ ድረስ መላው የዞኑ ህዝብ በተለመደው ትብብር እንዲጠባበቅ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የዞኑ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች