04/06/2026
የነገን ራዕይ በዛሬ ስትራቴጂ መቅረጽ
ዘመናዊው የአመራር ዓለም እንደ አውሎ ንፋስ በሚያልፉ ለውጦች የተሞላ ነው። በየቀኑ በምናየው የዲጂታልና የኢኮኖሚ መዋዠቅ ውስጥ አንድ መሪ የሚያስፈልገው ችሎታ ከዛሬው መትረፍ በላይ ነገን የመቅረጽ አቅም ነው። የነገን ራዕይ መገመት ብቻ ሳይሆን ያንን ራዕይ ወደ ተጨባጭ የድርጅት ጥንካሬ መቀየር የአመራር ጥበብ ቁንጮ ነው። አንድ መሪ በነገው ዓለም ውስጥ ተጫዋች ሳይሆን ፈጣሪ እንዲሆን የሚያደርጉት የወደፊት ግንዛቤ ዝግጁነት እና የድርጅት ጥንካሬ ናቸው።
የወደፊት ግንዛቤ የስትራቴጂያዊ ራዳር ነው። መሪው እንደ መርከብ ካፒቴን በአድማስ ላይ የሚታዩትን የቴክኖሎጂና የማህበራዊ ለውጦች ምልክቶች ቀድሞ መለየት አለበት። ዛሬ የምናያቸው ትናንሽ የለውጥ ጅረቶች ነገ ወደ ትልቅ ማዕበል እንደሚቀየሩ መረዳት መሪውን ከምላሽ ሰጪ ወደ ቀዳሚ አሳቢነት ያሸጋግረዋል። ይህ ግንዛቤ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን የፖለቲካና የኢኮኖሚ አዝማሚያዎች እንደ ራዳር በመከታተል ለውጥ ሳይመጣ መፍትሄን መፍጠር የሚቻልበት የስትራቴጂያዊ እይታ መድረክ ነው።
ማወቅ ብቻ ግን ለውጥን ለማሸነፍ በቂ አይደለም ዝግጁነት የአቅም ግንባታ ነው። የድርጅት ተለዋዋጭነት ወይም “Agility” ማለት ለውጥ ሲመጣ በፍጥነት የመቀየርና የመላመድ ብቃት ነው። ስልጠናዎችን በማካሄድ የሰው ኃይልን በየጊዜው ማደስ ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችል የብረት ጋሻ መፍጠር ነው። በተቋም ውስጥ ለወደፊት የኢኮኖሚ ተግዳሮቶችና ለዲጂታል ዘመን የሰው ኃይልን ማዘጋጀት የዝግጁነት ተግባር ነው። ይህ ማለት ድርጅቱ በአንድ ቦታ ላይ እንዳይቀዘቅዝ ሁልጊዜም እንደ አዲስ አምራች ኃይል ተለዋዋጭ መሆን አለበት።
የመጨረሻው ምሰሶ የወደፊት ጥንካሬ ነው። መዋቅርን ከማንኛውም ማዕበል ነፃ ማድረግ ማለት ድርጅትን በአንድ ሰው ወይም በአንድ የፖለቲካ አቋም ላይ ሳይሆን በሳይንሳዊ የአመራር መርሆዎች ላይ መገንባት ነው። ማዕበል ሲመጣ የሚሰበር ሳይሆን ይበልጥ ጠንካራ የሚሆን የስርዓት መዋቅር መፍጠር የጥንካሬ ምልክት ነው። ለወደፊት ፈተናዎች ዝግጁነት ድርጅትን ከማንኛውም የውጭ መናወጥ በላይ ከፍ የሚያደርገው የአመራር የላቀ ብቃት ነው።
በየእለቱ በሚደረጉ የሁኔታ ትንተናዎች (Scenario Planning) አማካይነት ለተለያዩ የወደፊት ሁኔታዎች ምላሽን ማቀድ ለለውጥ መዘጋጃ መንገድ ነው። እውቀትን በአንድ ክፍል ውስጥ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ዘርፎች መካከል በማጋራት የድርጅትን የመተጣጠፍ አቅም መፍጠር ይቻላል። ስልጠናዎችን ዘመናዊ በሆነ የኢንዱስትሪ መረጃ ማዘመን የወደፊት ጥንካሬን የመገንባት ስራ ነው። ዛሬ የምንገነባው የሰው ኃይልና መዋቅር፣ የነገውን ትውልድ በለውጥ ማዕበል ውስጥ ሳይሰበር እንዲያልፍ የሚያደርገው የአመራር አርክቴክቸር ነው።
መሪነት ማለት የነገውን አየር ሁኔታ ቀድሞ በማየት ዝናቡን ለመቋቋም ዝግጅት አድርጎ ማዕበሉ ሲመጣ የማይናወጥ ማዕከል መገንባት ነው። በለውጥ ፍጥነት ውስጥ የፋይናንስ አፈጻጸምንና ተፅእኖን ከሌሎች የተሻለ ለማድረግ የወደፊት ግንዛቤ መነጽር፣ ዝግጁነት የጦር መሣሪያ እና ጥንካሬ ደግሞ የድርጅቱ ቤተመንግስት መሆን አለባቸው። የዛሬን መሪነት ለነገው ድል መለወጥ የቻለ የለውጥ አድማስን መቆጣጠር ይችላል። ነገን የሚመሩ መሪዎች የዛሬውን ስኬት በነገው ራዕይ ውስጥ የሚቀርጹ ናቸው።
ዛዲግ አብርሃ
የአሌክስ ፕሬዝደንት