03/06/2026
የሁርሶ ዕጩ መኮንን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ታሪክ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ የዕጩ መኮነንነት ስልጠና ታሪክ የመጀመሪያው ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በ1927 ዓ.ም የተመሰረተው ሆለታ ገነት የሚገኘው የያኔው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጦር ትምህርት ቤት የአሁኑ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ አንዱ ሲሆን ሁለተኛው በ1950ዎቹ የተቋቋመው የሀረር ጦር ትምህርት ቤት ነው፡፡ ሶስተኛው የዕጩ መኮንን ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ደግሞ ከረዥም የሥልጠና ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና ካላቸው ማሰልጠኛ ተቋማት የሁርሶ ጦር ትምህርት ቤት ነው።
ከ1977 - 1983 ዓ.ም. ድረስ በነበሩት ስድስት ዓመታት ብቻ ለእናት ሀገራቸው አንድነትና ሉዓላዊነት መከበር ሲሉ ላባቸውን የጠመቁ፣ ደማቸውን ፣ያፈሰሱና አጥንታቸውን የከሰከሱ ከ22,000 ሽህ በላይ ጀማሪ መኮንኖች በማስመረቅ የጦር ሜዳ ጀግኖች አፍርቷል።
ይህ የማይረሳው፣ ፈፅሞ ፣የማይዘነጋው ስለ ዝነኛው የበረሃው የሥልጠና ማዕከል የሆነው የያኔው የሁርሶ ጦር ትምህርት ቤት የአሁኑ የሁርሶ እጩ መኮንን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ነው፡፡
የተነሳነው ከድሬዳዋ ከተማ በስተ ምዕራብ 30 ኪሜ. ርቀት ላይ፣ ከባሕር ወለል በላይ 1130 ሜትር ከፍታ ላይ ስለምትገኘው፣ በቀድሞው አጠራር በድሬዳዋ ኢሣና ጉርጉራ አውራጃ፣ በኋላም በድሬዳዋ ራስ ገዝ አሁን ደግሞ በሶማሌ ክልል ሺኒሌ ዞን አስተዳደር ሥር ስላለችው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ስለሚታፈስባት ሁርሶ ነው።
የሁርሶ ነዋሪዎች በዋናነት የሰርካማ ወንዝን በመጠቀም በመስኖ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በማልማት የሚተዳደሩ ሲሆኑ ከዚህ በተጨማሪ በአካባቢው የኢሳና የኦሮሞ አርብቶ አደሮች ይገኛሉ። ሁሉም በጋራና በፍቅር ተሳስበው ይኖራሉ፡፡
የ1969 ዓ.ም የዚያድ ባሬ የዕብሪት ወረራ የሶማሊያ ጦር ድሬዳዋ ከተማን በምዕራብ አቅጣጫ ለመክበብ ራሱ አስቀድሞ በአደራጃቸው ምንገደኞቹ በምዕራብ ሶማሌ ነፃ አውጭ ወንበዴዎች እየተመራ 1970 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ሰርጎ ገብ ጦሩን በሁርሶ ደቡብ ምዕራብ በሚገኘው የአሰሊሶና አሊቾ ተራራ ተረተር በኩል አስርጎ በማስገባት ወደ ኤረር ሸለቆ ተሻግሮ እስከ አዋሽ ድረስ በመዝለቅ የባቡር ሐዲዶችና ድልድዮች ላይ ጉዳት አደረሰ፡፡
በ1970 ዓ.ም አብዮታዊ ሠራዊት በመደበኛውና በሚሊሺያ ጦር ተጠናክሮ በጀግናው አየር ኃይላችን እየታገዘ በጠላት ላይ በወሰደው ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ፤ በድሬዳዋ ግንባር በጀልዴሣ፣ በሐረዋ፣በሁርሶ፣ በሐወሌ፣ በሺኒሌ፣ በሐመርካ፣ በአልባሕና በአይሻ መሽጎ ይርመሰመስ የነበረውን የሶማሊያ ወራሪ ሠራዊት እያሳደደ በመምታት ዳግም እንዳያንሰራራ አድርጎ አከርካሪውን ሰባብሯል።
ታሪኩ ወደ ሶማሊያ ወሰደን እንጅ ያለነው ሁርሶ ላይ ነው። ዋናው የወገን ኃይል በከፍተኛ ሞራልና ወኔ በማጥቃት ወደፊት ሲገሰግስ ቀሪው ደግሞ የኋላ ወረዳውን በአስተማማኝ ሁኔታ በማስጠበቅ በሁርሶ፣ጀልዴሳና ሺኒሌ ላይ ተጠናክሮ ተቀመጠ፡፡ በዚሁ ጊዜ በተዋጊ ኃይል ለተመናመኑ የወገን ጦር ክፍሎች ማሟያ የሚሆን ጦር ሁርሶ ላይ የማሠልጠን ሀሣብ ተወሰነ፡፡
ሁኔታው ከዚህም በላይ ርቆ በመጓዝ መንግሥት በተለይ የሁርሶ አካባቢ በረሃማ የአየር ፀባይ ለወታደራዊ ሥልጠና (ልምምድ) አመቺ ሆኖ ስላገኘውና በአቅራቢያውም የሰርካማ ወንዝ ያለማቋረጥ ከአመት እስከ አመት ስለሚፈስ የውኃ ችግር እንደማይኖር በመታመኑ፤ ሰላም ከተመለሰ በኋላ የተፈናቀሉትን የሁርሶ ነዋሪዎችን ወደ ሶደሬና ሌላም አካባቢ በማስፈር፤ ሁርሶ የቀደመ ታሪኩ ተለውጦ በርካታ የሠራዊት አባላትን የሚያስተናግድና የሚያሰለጥን ጦር ሠፈርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ሆነ፡፡
ይቀጥላል.......
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ድረ-ገፅ
https://dfmc.mod.gov.et/
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ዩቲዩብ
https://youtube.com/-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቴሌግራም
https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ
https://www.facebook.com/fdredefense.official