16/06/2026
የጤና አገልግሎት ማስታወቂያ ዝግጅትና ሥርጭትመመሪያ ቁጥር 1134/2018 የያዛቸው አንኳር ጉዳዮች
መግቢያ
የጤና አገልግሎት አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1362/2017 በጤናው ዘርፍ ያሉ አዳዲስ ጽንሰ-ሃሳቦችን አካቶ በመውጣት በሥራ ላይ ይገኛል። ከዚህ ጎን ለጎን አሁን ባለው የቴክኖሎጂ እና ማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ምክንያት አገልግሎት ሰጪ የጤና ተቋማት ወደ ማኅበረሰቡ የሚደርሱባቸው አማራጮች ሰፊ ናቸው። በመሆኑም ጤናን የተመለከተ የተሳሳተ ወይም የተጋነነ ማስታወቂያ በሰው ሕይወት ላይ ሊቀለበስ የማይችል አደጋ ከማስከተሉም ባሻገር በማኅበረሰቡ ዘንድ የተዛባ አመለካከት ይፈጥራል። አዋጅ ቁጥር 1362/2017 የጤና አገልግሎት ማስታወቂያን አስመልክቶ ዝርዝር መመሪያ እንደሚወጣ በአንቀጽ 48 ሥር የተደነገገ ሲሆን በዚህም መሠረት የጤና አገልግሎት ማስታወቂያ መመሪያ ቁጥር 1134/2018 ሊወጣ ችሏል። የመመሪያው ዓላማም የጤና አገልግሎት ማስታወቂያዎች ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ እንዲመሩ ማስቻል፣ የጤና አገልግሎት ማስታወቂያ የሚያዘጋጁና የሚያስተላላፉ አካላት ሙያዊ ሥነ ምግባርን የተከተለ እና የማኅበረሰቡን ባህል የጠበቀ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት የሚሉት ናቸው። በዚህ ጽሑፍ ቁጥጥር ስለሚደረግባቸው የጤና አገልግሎት ማስታወቂያዎች፣ የተከለከሉ ተግባራትና የሚያስከትሉት ተጠያቂነት በአጭሩ ይዳሰሳል።
የጤና አገልግሎት ማስታወቂያ ምንነት
የጤና አገልግሎት ማስታወቂያ ማለት ከጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የጤና ተቋም ስም፣ አርማ፣ የንግድ ምልክት ወይም ዓላማ እንዲተዋወቅ ለማድረግ በማስታወቂያ ማሰራጫ መንገድ አማካኝነት የሚሰራጭ ማስታወቂያ አንደሆነ በመመሪያው አንቀጽ 2(2) ሥር ተመልክቷል። ስለሆነም የጤና አገልግሎት ማስታወቂያ የጤና ተቋማት የሚሰጧቸውን የሕክምና እና ጤና እንክብካቤ አገልግሎቶችን በተለያዩ ዘዴዎች ማለትም በሕትመት አማራጭ፣ በስርጭት ማለትም በቴሌቪዥንና ራዲዮ እንዲሁም በዲጂታል ሚዲያ አማራጮች መረጃ የሚያሰራጩበት ዘዴ ነው።
የጤና አገልግሎት ማስታወቂያ ዝግጅት ታሳቢ ሊያደርጋቸው ስለሚገቡ ሁኔታዎች
የጤና አገልግሎት ማስታወቂያ ዝግጅት ታሳቢ ሊያደርጋቸው የሚገቡ ጉዳዮች በመመሪያ ተካተዋል፡፡ ይኸውም፡-
የቋንቋ አጠቃቀም
በመመሪያው አንቀጽ 4 መሠረት የጤና አገልግሎት ማስታወቂያ የታዳሚው ኅብረተሰብ
የሚናገረውን ቋንቋ እና አገላለጽ፣ አካል ጉዳተኞችንና ልዩ ፍላጎት ያላቸው የማኅበረብ ክፍሎችን ተጠቃሚነትና አካታችንት እንዲሁም አሻሚ ያልሆነ ወይም የሙያ ቃላት ያልበዙበት መሆን አለበት።
የይዘት /Content/
የጤና አገልግሎት ማስታወቂያ ይዘት የጤና ፖሊሲን ያከበረ፣ የማኅበረሰቡን ጤንነት ወይም ደህንነት የጠበቀ፣ መልእክቱ የሚተላለፍለትን ታዳሚ ታሳቢ ያደረገ፣ የማኅበረሰቡን ባህልና እሴት የጠበቀ እና አገልግሎቱ በጤና ተቋሙ ስለመሰጠቱ የሚያሳይ መሆን እንዳለበት በአንቀጽ 5 ተመልክቷል፡፡በተጨማሪም የጤና ተቋሙን ሥም፣ ደረጃ፣ በደረጃው መሠረት የሚሰጠውን አገልግሎት እና አገልግሎቱ የሚሰጥበትን አድራሻ ያካተተ መሆን አለበት። ጤና ተቋሙ ስላገኘው እውቅና ወይም ሽልማት የሚያስተዋውቅ ከሆነም ሽልማቱ ወይም እውቅናው የተሰጠበትን ጊዜ እና ምክንያት፣ ሽልማቱን የሰጠው ተቋም እና ስለ ሽልማቱ ያሉ ሌሎች መረጃዎችን ያካተተ መሆን አለበት፡፡
በአንፃሩ “የሁሉም ምርጫ”፣ “ተቀዳሚ ምርጫ” መሰል ግነት የበዛባቸው አገላለጾችን መጠቀም የለበትም። ከዚህ ጋር ተያይዞ የአንድ የጤና ተቋምን የጤና አገልግሎት ማስታወቂያ የሚያሰራጭ ወይም የሚያዘጋጅ ሰው የጤና ተቋሙ አግባብነት ካለው አካል የተሰጠ ሕጋዊ የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ያለው ስለመሆኑ የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት በመመሪያው አንቀጽ 13 ስር ተደንግጓል።
ሥነ-ምግባር /Ethics/
በመመሪያ አንቀጽ 6 መሠረት የቴና አገልግሎት ማስታወቂያ
• የሌሎች ጤና ተቋማትን አገልግሎት እና የጤና ባለሙያዎችን ክብር የማይነካ
• በጤና ተቋሙ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ከሌሎች ባለሙያዎች የተሻሉ እና የተለየ የሙያ ብቃትና እውቀት ያላቸው አስመስሎ ከመግለጽ የተቆጠበ
• አገልግሎት ለመስጠት ልዩ የሆነ ንጥረ ነገር እንደሚጠቀም ወይም የተለየ ፈውስ የሚገኝበት ተቋም እንደሆነ አስመስሎ የማይገልፅ
• ተገልጋዮች የጤና ተቋሙን አገልግሎት ካላገኙ በጤናቸው ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ የሚያሳይ (ፍርሃትን የሚፈጥር) አለመሆን
• የተገልጋይን ክብርና ሥነ-ልቦና የማይነካ እንዲሁም
• በዓለም ዓቀፍ እና በብሔራዊ ሕጎች ጥበቃ የሚደረግላቸውን እንደ ቀይ መስቀል፣ ቀይ ጨረቃ ወይም ቀይ ክሪስታል ሥሞች፣ አርማዎች ወይም ምልክቶችን ወይም የሌሎች ተቋማት፣ ሎጎዎች ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ሳይይር በቀጥታ ወይም አሳሳች በሆነ መልኩ የማይጠቀም መሆን ይጠበቅበታል፡፡
ምስክርነት /Testimony/
የጤና ተቋም የታካሚ ምስክርነትን የሚያካት ከሆነ በምስክርነት የሚሳተፈው ሰው ፈቃደኝነቱን በጽሑፍ መስጠትና በእርግጥም አገልግሎቱን በትክክል ያገኘ ሰው መሆን ያለበት ሲሆን በምስክርነት የሚሳተፈው ሰው ለአካላ መጠን ያልደረሰ ወይም የአዕምሮ ጤና ችግር ያለበት ወይም በራሱ መወሰን የማይችል ከሆነም ወላጅ፣ አሳዳጊ፣ ሞግዚት ወይም በሕግ ሥልጣን የተሰጠው ሰው የጽሑፍ ፈቃዱን መስጠት እንዳለበት በመመሪያው አንቀጽ 7 ተመልክቷል፡፡ በተጨማም የሚሰጠው ምስክርነት የተሰጠውን ህክምና የሚመለከት መሆን የለበትም፡፡
ሕጋዊ ክልከላዎችን መተላለፍ የሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነት
በአዋጅ ቁጥር 1362/2017 አንቀጽ 48 ሥር እንደተደነገገው የጤና አገልግሎት ማስታወቂያ በመገናኛ ብዙኃን ወይም በሌላ ዘዴ ሲተላለፍ ትክክለኛ፣ ተገቢ ወይም ወቅታዊ መሆን እንዲሁም የጤና ሙያን ሥነ ምግባር፣ የጤና ባለሞያውን ከብርና የሙያውን ሳይንሳዊ ይዘት የጠበቀ መሆን አለበት። እነዚህን ክልከላዎች መተላለፍ አስተዳደራዊ እና የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል ነው።
አስተዳደራዊ ቅጣት
በአዋጁ አንቀጽ 53 መሠረት በአዋጁ እና አዋጁን ተከትለው በሚወጡ ሕጎች የተደነገጉ ክልከላዎችን ተላልፎ መገኘት እንደተፈፀመው ጥፋት ክብደት ከማስጠንቀቂ ጀምሮ እስከ ፈቃድ መሰረዝ የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ ሊያስወስድ እንደሚችል የተደነገገ እንደመሆኑ ከጤና አገልግሎት ማስታወቂያ ጋር በተያያዙ ድንጋጌዎችን መጣስ አስተዳደራዊ ተጠያቂነት የሚያስከትል ይሆናል፡፡ በዚህም በመመሪያው አንቀጽ 11 መሠረት
• ክልከላ የተደረገባቸውን የቋንቋ፣ ይዘት እና ሥነ ምግባር መስፈርቶችን በመጣስ የጤና አገልግሎት ማስታወቂያ ያስተላለፈ ወይም እንዲተላለፍ ያደረገ የጤና ተቋም ከብር ከአስራ አምስት ሺ እስከ ብር ሀምሳ ሺ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ
• ፍቃደኝነቱን በጽሑፍ ያልሰጠ ወይም አገልግሎቱን በትክክል ያላገኘ ሰውን የጤና አገልግሎት ማስታወቂያ ላይ በምስክርነት ያሳተፈ የጤና ተቋም ከብር ሀያ ሺ እስከ ብር ሀምሳ ሺ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ
• አካለ መጠን ያልደረሰን ልጅ ወይም በራሱ መወሰን የማይችል ሰውን ከወላጅ፣ አሳዳጊ፣ ሞግዚት ወይም በሕግ ሥልጣን ከተሰጠው ሰው የጽሑፍ ፈቃድ ሳያገኝ በምስክርነት ያሳተፈ የጤና ተቋም ከብር ሀምሳ ሺ እስከ ብር መቶ ሺ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ የሚቀጣ ይሆናል፡፡
በተጨማም
• ማንኛውም አስተላላፊ የሚያስተላልፈው የጤና መረጃ ትክክለኛ ስለመሆኑ ከሚመለከተው አካል ሳያረጋግጥ ካስተላለፈ፣ መረጃው ወቅቱን የጠበቀ መሆኑን ሳያረጋግጥ ካስተላለፈ፣ ወቅታዊ የኅብረተሰብ የጤና አደጋና ወረርሽኝን ቅድሚያ መስጠትን ከጣሰ ከብር አስር ሺ እስከ ብር ሰላሳ ሺ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል።
የወንጀል ቅጣት
ምንም እንኳን መመሪያው አስተዳደራዊ ቅጣቶችን ብቻ የደነገገ ቢሆንም ክልከላዎችን መተላለፍ የወንጀል ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል በአዋጅ ቁጥር 1362/2017 አንቀጽ 55 (17) ሥር ተደንግጓል። በዚህም መሠረት ስለጤና አገልግሎት ማስታወቂያ የተደነገገውን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም
የጤና ባለሙያ ከ6 ወር በማያንስና ከ1 ዓመት በማይበልጥ እሥራት
የማስታወቂያ ድርጅት፣ የሚዲያ ተቋም ወይም የጤና ተቋም ከብር ሀምሳ ሺ በማያንስና ከብር አንድ መቶ ሺ በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል።
የቅሬታ አቀራረብና አፈታት
መመሪያውን ተመስርቶ አስተዳደራዊ ቅጣት የተወሰነበትና በውሳኔው ቅር ከተሰኘ አካል ከመመሪያ ጋር በተያያዘ ቅሬታ የሚቀርብበትን ሥርአት አስመልክቶ በፌደራል አስተዳዳር ሥነ ሥርአት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 በተመለከተው መሠረት ወይም አግባብ ባለው የክልል ሕግ መሠረት ውሳኔውን ለሰጠው አግባብ ያለው አካል ቅሬታውን ማቅረብ እንደሚችል በመመሪያው አንቀጽ 12 ሥር ተደንግጓል።
ማጠቃለያ
የጤና አገልግሎት ማስታወቂያዎች የሙያ ሥነ ምግባርን የተከተሉ፣ የሕክምና ሳይንሳዊ ሂደትን ያከበሩ፣ የማኅበረሰቡን ባሕልና እሴት የጠበቁ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በዚህ መነሻነትም የጤና አገልግሎት ማስታወቂያው ሊኖራቸው ስለሚገባው የቋንቋ አጠቃቀም፣ የይዘት እና የሥነ ምግባር ሁኔታ በመመሪያው የተደነገገ እንደመሆኑ የጤና ተቋማትም ሆኑ የጤና አገልግሎት ማስታወቂያ የሚያስተላለፉ አካላት በመመሪያው የተቀመጡ ጥብቅ መስፈርቶችን መከተል ይጠበቅባቸዋል።
በንቃተ ሕግና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ
የፍትሕ ሚኒስቴርን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆችን እና ድረ-ገፅን ይቀላቀሉ
Website
https://www.justice.gov.et
Facebook
https://www.facebook.com/MOJEthiopia/
(x) Twitter
https://x.com/MOJEthiopia
YouTube channel
https://youtube.com/...3701...
Telegram
https://t.me/fdreattorneyGeneral_externabo