02/06/2026
የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በሽያጭ/ በስጦታ ለማስተላልፍ በተመለከተ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች
ግንቦት 25 ቀን 2018 ዓ.ም
1) በስጦታ፣ በሽያጭ ወይም በሌላ መንገድ ተገልጋዮች ንብረት ለማስተላለፍ ሲመጡ ካርታው ከጀርባው የተረጋገጠ መሆን አለበት፡፡ ካርታው ዲጂታል ከሆነ የጀርባ ማህተም አያስፈልገውም፡፡
2) በካርታው ከጀርባ ላይ ንብረቱ በውርስ የተገኘና የወራሾች ዝርዝር የተፃፈበት ከሆነ ተጨማሪ ማስረጃ ማየት ሳያስፈልግ መስተናገድ ይችላሉ፡፡ ሆኖም የንብረቱ መለያ ተጠቅሶ ወራሾች መሆናቸው በደብዳቤ ከተገለጸ አገልግሎቱን መስጠት ይቻላል፡፡
3) በውርስ ወይም በስጦታ የተገኘ ንብረትን ለማስተላለፍ ወይም ለማከራየት የጋብቻ ማስረጃ አይጠየቅም፡፡
4) ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውጭ የተመዘገቡ የሚንቀሳቀሱም ሆነ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን የማስተላለፍ ወይም የማከራየት አገልግሎት ማግኘት የሚቻለው ንብረቶቹ በሚገኙበት ክልል/ከተማ አስተዳደር ነው፡፡ ስለሆነም በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የተቋሙ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ሊስተናገዱ አይችሉም፡፡ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤትም የሚያስተናግደው በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚመለከተው መ/ቤት የተመዘገቡ ንብረቶችን ብቻ ይሆናል፡፡
5) ከጋብቻ በፊት በተቋሙ ቀርበው የንብረት ማግለል ውል ያደረጉ ወይም በፍ/ቤት ያጸደቁ ተጋቢዎች ንብረታቸውን ለማስተላለፍ ወይም ለማከራየት ሲመጡ የትዳር አጋራቸው ስምምነት አያስፈልግም፡፡ ሆኖም የንብረት ማግለሉ ስምምነት አሁን ጸንቶ ካለው ጋብቻ የትዳር አጋር ጋር የተደረገ ሊሆን ይገባል፡፡
6) አካለ መጠን ላላደረሱ ልጆች ንብረት ለመግዛት ቢቻል ሁለቱም ወላጆች ሊገኙ ይገባል ፡፡ ካልሆነ አባት ወይም እናት ቀርበው መግዛት ይችላሉ፡፡ ሆኖም ከእናትና አባት ውጪ የሆነ ሞግዚት አካላመጠን ባላደረሰው ልጅ ስም ንብረት ለመግዛት በፍ/ቤት የተሰጠ ተጨማሪ ስልጣን ሊቀርብ ይገባል፡፡
7) አካለ መጠን ባልደረሰው ስም ተመዝግቦ የሚገኘውን የማይንቀሳቀስ ንብረት ለመሸጥ ሞግዚቱ እናትና አባትም ቢሆኑ በፍ/ቤት የተሰጠ ተጨማሪ ስልጣን ሊቀርብ ይገባል፡፡
8 ) ያላገባ ማስረጃ ላይ ቀደም ሲል ጋብቻ ስለመኖሩ የሚጠቁም የጊዜ መረጃ ሲኖር ንብረቱ በጋብቻ ወቅት የተፈራ ሊሆን ስለሚችል ንብረቱ የተፈራበትን ጊዜ የሚያመለክት ከሚመለከተው አካል የተሰጠ ተጨማሪ ማስረጃ ሊቀርብ ይገባል፡፡
9) ተነጻጻሪ ካርታ ማለት በአንድ የቦታ ስፋት ውስጥ የተለያዩ ቤቶችና ባለመብቶች ያሉበትና በተለያዩ ሰዎች ሊያዝ የሚችል ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ይዞታ ላይ የባለቤትነት መብት ያለው ሰው የራሱን ካርታ በመያዝ ድርሻውን ጠቅሶ መሸጥ ይችላል፡፡
10) ካርታ ላይ የሚጠቀሰው ቀን ካርታው የተሰጠበትን ቀን እንጂ ንብረቱ የተፈራበትን ቀን በቀጥታ ላያመለክት ይችላል፡፡ ስለሆነም ንብረቱ የተፈራበትን ቀን ለማወቅ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የንብረቱ ባለቤት ተጨማሪ ማስረጃ እንዲያቀርብ መደረግ አለበት፡፡ ለምሳሌ ከመሬት አስተዳደር ለገቢዎች እና ለካርታው ባለቤት የሚሰጡ ደብዳቤዎችን አያይዞ መስራት ይቻላል፡፡
11) የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረትን በሽያጭም ሆነ በስጦታ ለማስተላለፍ የፍቺ ውሳኔ ይዘው የሚቀርቡ ባለጉዳዮች ንብረቱ የጋራ ወይም የግል ስለመሆኑ በፍርድ ቤት የጸደቀ የንብረት ክፍፍል ስምምነት ወይም ውሳኔ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡
12) ንብረት በስጦታ ለማስተላለፍ የተሠጠ የውክልና ሥልጣን ስጦታው ለማን እንሚሰጥ እና ንብረቱ ምን አይነት እንደሆነ በውክልናው ላይ በግልፅ መቀመጥ አለበት፡፡ ነገር ግን በውክልና ስጦታ ለመቀበል ሲሆን ስጦታ ይቀበልልኝ የሚለው አገላለጽ በቂ ነው፡፡
13) የጋራ ንብረት በሽያጭ በሚተላለፍበት ጊዜ ገዢው ከንብረት ተጋሪው ውጪ የሆነ እንደሆነ የተጋሪው የቅድሚያ መግዛት መብት መጠበቁን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም የማይንቀሳቀስ ንብረት ሲሆን ተጋሪውን ምስክር በማድረግ፣ የሚንቀሳቀስ ንብረት ሲሆን ተጋሪው ማረጋገጫ እንዲሰጥ ማድረግ ይቻላል፡፡
14) የማይንቀሳቀስ ንብረት ገዢው የውጭ ሃገር ዜጋ ከሆነ የታደሰ በትውልድ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ ወይም በኢንቨስትመንት አዋጁ መሠረት ቢያንስ አሥር ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ በሥራ ላይ ማዋሉን የሚገልጽ ማስረጃ እና የኢንቨስትመንት ፈቃድ ሊቀርብ ይገባል፡፡
15) የማይንቀሳቀስ ንብረት ገዢው የውጭ ሃገር ዜጋ ሌላ የመኖሪያ ቤት በስሙ የሌለ መሆኑን የሚገልጽ ከሚመለከተው የንብረት መዝጋቢ አካል ማስረጃ መቅረቡን እንዲሁም ከተቋሙ የመረጃ ቋት መጣራት ያስፈልጋል፡፡