31/05/2026
በኢትዮጵያና በቤልጂየም መካከል ያለው የከፍተኛ ትምህርት አካዳሚክ ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደረገ።
-------------------------- // -----------------------
(ግንቦት 23/2018 ዓ.ም) የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፉ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ በኢትዮጵያ የቤልጅየምን አምባሳደር የሆኑትን ዶ/ር አኔሊስ ቬርስቲቼልን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በዚሁ ጊዜ በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ እየተተገበሩ ስላሉ ዋና ዋና የሪፎርም ተግባራት ለክብርት አምባሳደሯ አብራርተዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል በትምህርት መስክ በሰው ኃይል ልማት ፣ በጥናትና ምርምር ፣በልምምድ ልውውጥና በሌሎችም ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ የትብብር ግንኙነቶች መኖሩን አንስተዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር የዩኒቨርስቲ ራስገዝነትን ጨምሮ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጥራት፣ ብቃትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያና ጅቡቲ የቤልጂየም አምባሳደርና የአፍሪካ ሕብረት የኢጋድና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቋሚ ተወካይ ዶክተር አኔሊስ ቨርስቲቼል በበኩላቸው በኢትዮጵያና በቤልጂየም መንግስታት መካከል 120 ዓመታትን ያስቆጠረ ወዳጅነትና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መኖሩን ተናግረዋል።
በተለይም በከፍተኛ ትምህርቱ ዘርፍ ባለው የትብብር ግንኙነት ባለፉት ዓመታት በርካታ ኢትዮጵያውያን በቤልጂየም ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ነጻ የትምህርት እድል ተጠቃሚ እንደሆኑ አብራርተዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ያለው የአካዳሚክ ትብብር ለወደፊቱም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አገራቸው በጋራ መሥራት እንደምትፈልግም ዶ/ር አኔሊስ ተናግረዋል።
በመጨረሻም ሁለቱ ወገኖች በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ያለውን የአካዳሚክ ትብብር በምርምር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በመምህራንና ተማሪዎች ልውውጥ እንዲሁም በአቅም ግንባታ መስኮች የበለጠ ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን በሚከተሉት ማስፈንጠሪያዎች ያግኙ፡-
በፌስቡክ -https://www.facebook.com/fdremoe/
በቴሌግራም -https://t.me/ethio_moe
በትዊተር - http://twitter.com/fdremoe
ዩቱዩብ- https://www.youtube.com/-of-education-ethiopia
በሊንክዲን - https://www.linkedin.com/.../ministry-of-education-ethiopia
በዌብሳይት - www.moe.gov.et ይከታተሉ