04/06/2026
የጤና መድህን አስተማማኝ ጋሻ እና ድልድይ
28/09/2018 ዓም ኢጤመአ
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ስር በሚገኝ አንድ ምስኪን ጎጆ ውስጥ፣ ህይወት በፈተና እና በውጣ ውረድ የተሞላች ነበረች። ወይዘሮ የሺ ጌታነህ ከአንድ ልጃቸው እና ከባለቤታቸው ጋር የሚኖሩ የዕለት ጉርሳቸውን ለማሟላት በቀን ስራ የሚደክሙ ጠንካራ እናት ናቸው። ነገር ግን፣ በአንድ ወቅት በቤተሰባቸው ላይ ድንገት የተጋረጠው ከባድ ፈተና የኑሯቸውን ምሰሶ ሊነቀንቀው፣ ተስፋቸውንም ሊያጨልመው ተቃርቦ ነበር።
ማዕበሉ የጀመረው የቤተሰቡ እራስ በሆኑት በባለቤታቸው ድንገተኛ መታመም ነበር። ጥበቃ ስራ ተቀጥረው መስራት ጀምረው ገና አንድ ወር እንኳ ሳይሞላቸው ነበር ህመሙ ከአልጋ የጣላቸው። ያኔ ወይዘሮ የሺ፣ የባለቤታቸው ህይወት በአስጊ ሁኔታ ውስጥ መውደቁንና በወቅቱ የተሰማቸውን የፍርሃትና የሰቀቀን ስሜት ዛሬም ድረስ በቅዠት አዘል ትውስታ ያስታውሱታል።
የባለቤታቸው ጤና እያሽቆለቆለ ሲሄድ፣ ወይዘሮ የሺ ግራ በመጋባትና በጭንቀት ተከበው በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ አቀኑ። ሆኖም የህመሙ ክብደት ከጤና ጣቢያው አቅም በላይ በመሆኑ፣ በሌሊት ሰባት ሰዓት ላይ በጭለማው መሃል ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ይዘውት ለመምጣት ተገደዱ። በሆስፒታሉ ግድግዳዎች መሃል የተስፋና የጭንቀት ቀናትን እየቆጠሩ ዘጠኝ ቀናት ነጎዱ።
ለእነ ወይዘሮ የሺ፣ የዕለት ኑሮን መግፋት ቀርቶ የቤት ኪራይ መክፈል ራሱ እንደ ተራራ የከበደ የዘወትር ፈተናቸው ነው። በእንዲህ ያለ አቅም አጥቶ የመጨነቅ አዙሪት ውስጥ፣ ታሞ የተኛን ሰው በከፍተኛ የህክምና ተቋም ውስጥ ማከም ለእነሱ ማሰብ እንኳ የማይቻል ህልም ነበር። ወይዘሮ የሺ ያንን የጭንቀት ወቅት ሲያስታውሱ፣ የጤና መድህን ባይኖር ኖሮ ባለቤታቸው ቤት ውስጥ ከመሞት ውጪ ሌላ አማራጭ እንዳልነበራቸው በቁጭት ይገልጻሉ። ወደ ህክምና ተቋም የሚመጡበት አምስት ሳንቲም እንኳ በእጃቸው አልነበረም። እንዲያውም ሆስፒታል ውስጥ የነጻ ምግብ አገልግሎት መኖሩን ሳያውቁ፣ ምንም ሳይቀምሱ ውለው ያደሩባቸው የረሃብና የጭንቀት ቀናት ነበሩ። በኋላ ግን በሆስፒታሉ ሰብአዊ ድጋፍ ምግብ ማግኘት በመቻላቸው ያንን ከባድ ቀን ሊሻገሩት ችለዋል።
በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በቆዩባቸው በእነዚያ ዘጠኝ ቀናት፣ ባለቤታቸው አስፈላጊው ምርመራ ሁሉ ተደርጎለት የጨጓራ እና የደም ማነስ ህመም እንዳለበት ተረጋገጠ። በአሁኑ ወቅትም ተገቢውን ህክምና እና ክትትል እያገኘ፣ የጤናው ሁኔታ በፍጥነት ወደ ተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል።
"ለመሆኑ ይህ ሁሉ የህክምና ወጪ እንዴት ሊሸፈን ቻለ?" የሚለው ጥያቄ ሲነሳ፣ የወይዘሮ የሺ ምላሽ የጤና መድህን ለዜጎች፣ በተለይም አቅም ለሌላቸው ወገኖች ያለውን የላቀ እና ህይወት አዳኝ ፋይዳ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። ወይዘሮ የሺ በኩራትና በምስጋና መንፈስ፦ "የጤና መድህን አለኝ፤ እስካሁን ድረስ አንድም ሳንቲም ክፍያ አልተጠየቅኩም። የጤና መድህን የባለቤቴን ህይወት እየታደገው ነው" በማለት ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።
ይህ ታሪክ የአንድ ቤተሰብ ምስክርነት ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የጤና መድህን አገልግሎት በጭንቀትና በችግር ማዕበል ውስጥ ለሚወድቁ ምስኪን ዜጎች እንዴት ያለ አስተማማኝ ጋሻ እና ድልድይ መሆኑን ያረጋገጠበት እውነተኛ ማሳያ ነው እንጂ።"Youtube: https://www.youtube.com/-HealthInsurance
Website: www.ehis.gov.et
Twitter: http://twitter.com/service4E
Facebook: https://web.facebook.com/EthioHIS/
Telegram: https://t.me/buuu1lTelegram: https://t.me/buu
X (formerly Twitter) (https://twitter.com/service4E)
Ethiopia Health Insurance Service () / X