31/03/2026
"ከሀገራችን አልፎ ለአፍሪካና ለሌሎችም ሀገራት ጭምር ሞዴል በሆነ ተቋም ውስጥ ህዝብና መንግስትን ማገልገል መቻል ትልቅ ዕድል ነው" ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ርስቱ ይርዳው
*************
መጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ርስቱ ይርዳው ከሀገራችን አልፎ ለአፍሪካና ለሌሎች ሀገራት ጭምር ሞዴል በሆነ ተቋም ውስጥ ሕዝብና መንግስትን ማገልገል መቻል ትልቅ ዕድል ነው ያሉት በጠቅላይ መምሪያው በተዘጋጀ የአቀባበልና የትውውቅ መርሃ-ግብር ላይ ነው።
ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሀገራችን የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ሪፎርም ውስጥ ግንባር ቀደም የሆነ ለውጥና ዕድገት በማስመዝገብ ዘመኑን የዋጀ የፖሊስ አገልግሎት በመስጠት የሀገር ኩራትና መከታ፤ የህዝባችን የክብር መገለጫ እየሆነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ተቋሙ በልዩ ሁኔታ በተግባሩና በአስተሳሰቡ የገዘፈ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀ፣ ሙያዊ ተልዕኮውን በሚገባ ያወቀና የተረዳ፣ ዜጎች በአለኝታነት የሚተማመኑበት ተወዳዳሪ ተቋም መሆኑን አንስተዋል። በተለይም በሰብዓዊ መብት አያያዙ በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር የተመሰከረለት መሆኑንም ተናግረው ውጤቱም የአመራሩና የመላው ሠራዊት ሀገርን የማገልገል ከፍተኛ ቁርጠኝነት ውጤት እንደሆነም ገልፀዋል።
ክቡር ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዕድገትና ለውጥ ቀጣይነት ያለው በመሆኑ የተመዘገበው ስኬት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ በዲስፕሊንና በሙያዊ ክህሎቱ የተመሰገነ እና ከሀገር የተሻገረ ዕውቀት ያለው ሠራዊት ለመገንባት ከፍተኛ አመራሩ በበለጠ በጋራና በትብብር ተቀናጅቶ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ ክቡር አቶ ሙሊሳ አብዲሳ በበኩላቸው፤ ባለፉት ሰባት የሪፎርም ዓመታት በተሰራው ጠንካራ ሥራ በወንጀል ምርመራ ላይ ይቀርብ የነበረውን ከፍተኛ ቅሬታ በመቅረፍ ተጠያቂነት ያለው አሠራር መዘርጋቱን ጠቅሰው፤ ሕግን አክብሮ የሚያስከብር ፕሮፌሽናል የፖሊስ አገልግሎት ለመስጠትና የተመዘገበውን ዕድገት ለማስቀጠል ከፍተኛ አመራሩ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የጠቅላይ መምሪያው ተጠሪ ምክትል ዋና መምሪያዎችና መምሪያዎች የስድስት ወር የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።