18/09/2026
በትጉህ ልጆቿ የቱሪስት መዳረሻዎቿን ያበራከተች ህብረ ብሄራዊት ከተማ! አዲስ አበባ!
በስም ብቻ አብባ የቆየችው አዲስ አበባ ከጥቂት ዓመታት በፊት የቱሪስት መሸጋገሪያ እንጂ መዳረሻ እንዳልነበረች ይታወሳል፡፡
ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ለቱሪስት መስህብነት ጎላ ብለው የሚጠቀሱ መዳረሻዎች ብዙም አልነበሯትም፤ የነበሩት ዕድሜ ጠገብ ቅርሶቿም ቢሆኑ አስታዋሽ ስላልነበራቸው የህልውና አደጋ ተጋርጦባቸው ቆይተዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ(ዶ/ር) የገበታ ለሸገር ኢኒሸቲቭ አንፀባራቂ ጉዞውን የጀመረው የከተማችን ለውጥ ነባር ቅርሶችን በማደስ ዘመን ተሻጋሪ ገፅታን እንዲላበሱ አስችሏል፤ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማበራከትም መዲናችን የስዕበት ማዕከል አድርጓታል፡፡
ከፍተኛ የሆነ የፅዳት ጉድለት የነበረበትንና የተለያዩ የውንብድና ወንጀሎች ጭምር ሲፈፀሙበት የነበረውን ‹‹እሪ በከንቱ›› ይባል የነበረውን አካባቢ የወዳጅነት አደባባይ እና የወዳጅነት ፓርክ በመገንባት ለህፃናት መጫዎቻ፣ ለሰርግ እና መሰል ሁነቶች ድምቀት እንዲሁም የሀገር ውስጥ እና የውጭ ዜጎች የስዕበት ማዕከል ማድረግ ተችሏል፡፡ በአቅራቢያውም ግዙፉ የአብርሆት ቤተ መፅሀፍት በመገንባቱ የተማሪዎች፣ የተመራማሪዎች እና የሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች የዕውቀት ማዕድ ሆኗል፡፡
መሀል ከተማ ላይ ቢሆንም ከነዋሪዎች እርቆ የቆየው ቤተ መንግስትም ከተደረገለት ዘመን ተሻጋሪ እድሳት ባሻገር በግቢው ውስጥ ግዙፉ የአንድነት ፓርክ በመገንባቱ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ዜጎች የቱሪስት መስህብ መሆን ችሏል፡፡
በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎች ጭምር በስም እንጅ በአካል የማያውቁት እንጦጦ እና አካባቢውም ዋነኛ የስዕበት ማዕከል መሆኑ መጀመሩ በየቀኑ የሚታይ እውነታ ነው፡፡ በአካባቢው ‹‹እንጨት በመሸከም›› ይተዳደሩ የነበሩ እናቶችም፣ ህይወታቸውን በዘላቂነት ለመቀየር በተገነባላቸው የእንጀራ ፋብሪካ፣ የኑሮ ደረጃቸው ከፍ ማለት ጀምሯል፡፡
በእንጦጦ ፓርክ አዲስ ገፅታን መላበስ የቻለው እንጦጦ ተራራ እና አካባቢው የሁለት ግዙፍ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች መነሻ በመሆኑም የስዕበት ማዕከልነቱ በእጅጉ ጨምሯል፡፡ ንፁህ አየር የሚቀበሉ አረጋውያን፣ የሚቦርቁ ህፃናት፣ ልምምዳቸውን የሚሰሩ አትሌቶች፣ የተለያዩ ቀረፃወችን የሚያደርጉ አርቲስቶች፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ወጣቶችና ታዳጊዎች እንዲሁም የውጭ ሀገር ዜጎች ከእንጦጦ እስከ መሀል ከተማ በተገነቡ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች ላይ ሲዝናኑ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡
መነሻቸውን ከእንጦጦ ተራራ በማድረግ እስከ ፒኮክ መናፈሻ እንዲሁም እስከ ቀበና ወንዝ የተገነቡት የወንዝ ዳር ፕሮጀክቶች ከተማችን ለቱርስት መዳረሻነት ያላትን ዕምቅ አቅም ከፍ አድርገው አሳይተዋል፡፡
የሁሉም ጥቁር ህዝቦች የድል ምልክት ተደርጎ የሚወሰደውን፣ በአባት እናቶቻችን የህይወት መስዋዕትነት የተመዘገበውን፣ የአድዋ ድልን ለመዘከር የተገነባው የዚህ ትውልድ አሻራ፣ ግዙፉ የአድዋ ድል መታሰቢያ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ጎብኝዎች የሚጨናነቅ የከተማችን እንዲሁም የሀገራችን ምልክት ሆኗል፡፡
የአፍሪካ፣ የእሲያ፣ የአውሮፓ እና በሌሎችም አህጉራት የሚገኙ ሀገራት መሪዎች ወደ ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ ሲመጡ የአበባ ጉንጉን በክብር የሚያስቀምጡበት፣ ዓለም አቀፍ የስዕበት ማዕከል በመሆኑ የአድዋ ድል መታሰቢያ የሁላችንንም ልብ የሚያሞቅ አኩሪ ታሪክ ነው፡፡
ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሚመች መልኩ የተገነባው ለሩጫም፣ ለመዝናኛም ፣ ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ለስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና ውድድሮች አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ግዙፉ የአድዋ ፓርክም ጥራትን ከስፋት፣ ውበትን ከአካታችነት ጋር አጣምሮ የያዘ ግዙፍ የቱሪስት መዳራሻ መሆኑን መመልከት ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ያደረጉ፣ በሀገር ፍቅር ስሜት የብሔራዊ መዝሙራችንን እየዘመሩ የሀገር ፍቅር እንባቸውን ያፈሰሱ ጀግኖቻችንን የሚዘክሩ ገላጭ ሀውልቶችን የያዘውና የተለያዩ ስፖርታዊ ክንውኖችን የሚያስተናግደው የስፖርት ፓርክም የብዙዎችን ቀልብ እየሳቡ ከሚገኙ የመዲናዋ የቱሪስት መስህቦች ውስጥ ይጠቀሳል፡፡
የአዲስ አበባን የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከልነት እውን ለማድረግ በመፍጠር እና በመፍጠን የተገነባው ግዙፉ አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከልም ታሪካዊውንና 4ሺህ አካባቢ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበትን ሀገራዊ ምክክር ጨምሮ ታላላቅ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ መድረኮችን በስኬት ማስተናገድ አስችሏል፡፡
ባለፈው ዓመት ብቻ 221 ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ኮንፈረንሶችን ያስተናገደችው አዲስ አበባ ከቱሪስት መዳረሻነት በተጨማሪ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል የመሆን ጅምሯ የሰመረ መሆኑን አመላካች ነው፡፡
የቱሪስት መዳረሻዎችን እያበራከተች የምትገኘው መዲናችን አዲስ አበባ መስቀል አደባባይን ደረጃውን በጠበቀ አግባብ እንደ አዲስ በመገንባት የመስቀል ደመራን አከባበር ደማቅ ገፅታ እንዲላበስ አድርጋለች፡፡
የኢሬቻ በዓልን እሴቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት እንዲከበር ያስቻለው ግዙፉ ኢሬቻ ፓርክም ሚሊዮኖች የሚሰባሰቡበት የከተማችን የቱሪስት መዳረሻ ነው፡፡
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት