03/06/2026
የጅማ-ጭዳ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በተሻለ አፈፃፀም ላይ ይገኛል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2018 (ኢመአ)፦በኦሮሚያና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትስስር ይበልጥ የሚያሳድገው የጅማ - ጭዳ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በተሻለ አፈፃፀም ላይ ይገኛል ።
80 ኪሎሜትር በሚረዝመው የመንገዱ ግንባታ አፈፃፀም የአፈር ጠረጋ ፣ የውሃ ማስወገጃ ፉካዎችና የስትራክቸር ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን የፕሮጀክቱ 27.12 ኪሎ ሜትር የሚሆነው መንገድም በአስፋልት ንጣፍ ተሸፍኗል። ይህም አጠቃላይ አፈፃፀሙን 49.31 በመቶ አድርሶታል።
ከ2.4 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የተመደበለት የመንገዱ ግንባታ በቻይናው ቲሲጁ ሲቪል ኢንጅነሪንግ ግሩፕ አማካኝነት በመከናወን ላይ ነው።
የፕሮጀክቱን የማማከርና የቁጥጥሩን ሥራ ደግሞ ኪዮንግዶንግ ኢንጅነሪንግ ፣ ኦረንትያል ኮንሰልቲንግ ግሎባል እንዲሁም ኮር ኮንሰልቲንግ ኢንጅነርስ በጋራ በመሆን እያከናወኑ ይገኛሉ።
የግንባታው ሙሉ ወጪ ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከጃፓን ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅት (JICA) በተገኘ ድጋፍ የተሸፈነ ነው።
የወሰን ማስከበር ችግሮች፣ የግንባታ ግብዓት አቅርቦት እጥረት ፣ የሥራ ተቋራጩ የአፈፃፀም ውስንነት እና የነዳጅ እጥረት በግንባታው ሂደት ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሮ ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሮችን ለመቅረፍ እና ግንባታውን ለማፋጠን በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
የጅማ ጭዳ መንገድ ሲጠናቀቅ እንደ ቡና ፣ ሰሊጥና የተለያዩ ፍራፍሬዎች እንዲሁም የግብርና ምርቶችን ወደ ገበያ ማዕከላት ለማድረስ የሚያስችል ነው።
እንዲሁም ወደ ኮይሻ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የሚደረገውን የተሽከርካሪ ጉዞ ለማቀላጠፍና በአካባቢው የሚመረተውን የድንጋይ ከሰል በቀላሉ ለማጓጓዝ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡
በተጨማሪም ለጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክና ለሃላላ ኬላ የቱሪስት መስህቦች አማራጭ መሄጃ በመሆኑ የአካባቢውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንደሚያሳድግ ይጠበቃል።
በተጨማሪ
› አጭር መልዕክት 8561
› ፖስታ ሳጥን ቁጥር 1770
› ድህረገጽ www.era.gov.et
› ፊስቡክ https://www.facebook.com/www.era.gov.et
› ቴሌግራም https://t.me/ethioroads
› ትዊተር https://twitter.com/EthiopiaRoadsAd
› ኢንስታግራም https://www.instagram.com/ethioroads
› ኢሜል [email protected]
› ዩቲዮብ www.youtube.com/