15/09/2026
አረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት ዓለም አቀፍ ትብብር ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ
የኖርዲክ–አፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በኢትዮጵያ ሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ነው።
መስከረም 5/2019 ዓ.ም (ትሎሚ) — የአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመቋቋም፣ የአማቂ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስና ዘላቂ የልማት አማራጮችን ለማስፋፋት አረንጓዴ ትራንስፖርትን ማሳደግ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።
ጉባኤው በኖርዲክ ሀገራትና በአፍሪካ መካከል በአካባቢ ጥበቃ፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ በታዳሽ ኃይልና በዘላቂ ትራንስፖርት ዘርፎች ያለውን ትብብር ለማጠናከርና ለአየር ንብረት ለውጥ ተግባራዊ መፍትሔዎችን ለማፍራት ያለመ ነው።
በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አለሙ ስሜ፣ የአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመቋቋም አረንጓዴ ትራንስፖርትን ማስፋፋት የጋራ ጥረትን የሚጠይቅ በመሆኑ የዓለም አቀፍ ትብብር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የፋይናንስ ድጋፍ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም የአማቂ ጋዝ ልቀትን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት፣ የታዳሽ ኃይል አጠቃቀምንና ዘላቂ የትራንስፖርት ሥርዓትን ማጠናከር እንዲሁም ከካርቦን ነፃ የኃይልና የትራንስፖርት አማራጮች ላይ የጋራ ኢንቨስትመንት ማድረግ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በተለይም ለአረንጓዴ ትራንስፖርት ሽግግር የሚያስፈልጉ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ አቅሞችን ማሳደግ፣ የእውቀትና የተሞክሮ ልውውጥን ማጠናከር እንዲሁም የጋራ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ማስፋፋት የጋራ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የኖርዲክ–አፍሪካ ትብብር ከአካባቢ ጥበቃና ከአየር ንብረት ለውጥ ባሻገር በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በዲጂታላይዜሽንና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ላይም ያተኮረ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል።
በዚህ መሠረት የግል ዘርፉን በማጠናከር የጋራ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራዎችን ማበረታታት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን መገንባት በትብብሩ ውስጥ ትኩረት የሚሰጣቸው ዋና ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቁሟል።
በጉባኤው በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሽግግርና በአረንጓዴ ትራንስፖርት ዙሪያ የፓናል ውይይቶችም ተካሂደዋል።
ኢትዮጵያም የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማበረታታት የወሰደቻቸውን የፖሊሲ፣ የስትራቴጂና የስታንዳርድ እርምጃዎች እንዲሁም በኤሌክትሪክ ትራንስፖርት ሽግግር ያላትን ተሞክሮ ለተሳታፊዎች አጋርታለች።
የኖርዲክ–አፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤው ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይና አይስላንድን ጨምሮ የኖርዲክ ሀገራትና የአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር በአየር ንብረት፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚና በዘላቂ ትራንስፖርት ዘርፎች የጋራ መፍትሔዎችን ለማምጣት የሚያግዝ መድረክ መሆኑ ተገልጿል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር መረጃዎችን ለማግኘት👇👇👇
በድረ ገጽ፡
www.motl.gov.et
በፌስቡክ
https://www.facebook.com/EthiopianTransport?mibextid=ZbWKwL
በቴሌግራም:
https://t.me/ministryoftransportethiopia
በዩቲዩብ
https://youtube.com/
በትዊተር
https://x.com/MoTLogestics
በቲክቶክ
https://www.tiktok.com/?_r=1&_t=ZS-93fuvA1twuuy