08/06/2026
የስርዓተ-ምህዳር ግልጋሎት (PES) ክፍያ አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት አስፈላጊ መሆኑን ተገለጸ፡፡
አዲስ አበባ
*************************************************************************************************
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ እና ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የስርዓተ-ምህዳር ግልጋሎት(PES) ክፍያ አዋጅ ቁጥር 1401/2017 በሚመለከት የባለድርሻ አካላት ውይይት ተካሄደ፡፡ የዕለቱ ውይይት በዋናነት በአየር ንብረት ለውጥ እርምጃዎች እና ውጤቶቹ እንዲሁም በስርዓተ ምህዳር ግልጋሎት ክፍያ ላይ ያተኮረ ሲሆን መድረኩን ዓለማቀፍ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የምርምር ዩኒቨርስቲዎች፣ ኢምባሲዎች እንዲሁም የፌዴራል ተቋማት ተሳትፈውበታል፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ንጉሥ ለማ መርሃ-ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት በሀገራችን እየተተገበሩ እንደ አረንጓዴ አሻራያሉ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ሀገራችን እና ህዝባችን የሚገጥሟቸው ግዙፍ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ከሚደረጉ ጥረቶች ማሳያ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ኃላፊው አክለውም የአካባቢ ጥበቃ ተፈጥሮን ከመጠበቅ ባለፈ የምግብ ዋስትናን፣ የኑሮ ሁኔታን፣ የልጆቻችንን ደህንነት፣ ሰላም እና የሀገራችንን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስን መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የስርዓተ-ምህዳር ግልጋሎት ክፍያ (PES) አዋጅ ቁጥር 1401/2017፡ ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር ብርቱ ጥረት እያደረገ መሆኑን እና ለወደፊት ከሌሎች ዘርፍ መስሪያ ቤቶች ጋር በቅንጅት ለመስራት ቁርጠኛ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ የወርልድ ቪዥን ዳይሬክተር ካርመን ቲል በበኩላቸው ተቋማቸው መሬትን መልሶ ማልማት (restoration) ላይ ትኩረት በማድረግ እየሰራ እንደሆነ ገልፀው ይህም ዛፍ መትከል ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ስለ መሬት፣ ውሃ፣ የኑሮ ሁኔታ፣ የአካባቢ ተቋማት፣ እንዲሁም ስለ ህጻናት እና ማህበረሰቦች መጻኢ እድል ጭምር ማሰብ እና መስራት መሆኑን በመድረኩ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በቀጣይ የተሳካ ውጤት እንዲመዘገብ በስርዓተ ምህዳር ግልጋሎት አቅራቢዎች እና ተጠቃሚዎች መካከል ግልፅ የሆነ የአሰራር ስርዓትን በማስፈን ከመስኩ የሚገኘውን ትሩፋት ለማላቅ ከፍተኛ ጥረት መደረግ እንዳለበት ገልፀዋል፡፡
የዕለቱ መርሀግብር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት በሚቻልባቸው ነጥቦች ዙሪያ በመወያየት የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ተፈጽሟል፡፡