04/10/2016
★★★ ኤሎሄ ኤሎሄ ★★★
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
የሀገሬ ችግር የወገኖቸ ሞት
እያደር ቢጨምር፣
ባንዱ ባንዱ ምክንያት ግፉ ቢጠነክር፣
ያሳለፍነው አመት ያደረሰብንን
ያፈሰሰውን ደም፣
ጦሱን ይዞ እንድያልፍ በአድሱ አመትም
ዳግም እንዳይደግም፣
ፈጣሪን ተማፅነን ባንድነት ለምነን፣
እጅ ለእጅ ተያይዘን ሰላምን ለማብሰር
ምለን ተማምለን፣
አድሱን አመትም ገና እንደጀመርነው፣
ወርሃ መስከረምን በፍቅር እንደጀመርን
ገና ሳንጨርሰው፣
ልብን የሚሰብር ሀዘን ሰማን ምነው?፣
ክቡሩ የሰው ልጅ በዚች በኛ ምድር
ምነው ረከሰ?፣
የዜጎች ንፁህ ደም እንደ ክረምት ውሃ
በከንቱ ፈሰሰ፣
በሀዘኑ ምሬት ውስጤን እጅግ ከፋው
አይኔም አለቀሰ፣
መከራው ሲጨምር በወገኖቸ ሞት
ሆደ ተላወሰ፣
አምናና ታች አምና በደረሰው ሀዘን
ልቤ ሳያገግም፣
ያም አልበቃ ብሎ ዛሬ ላይ ሲደገም፣
ምነው አላለቅስ ልቤ እንደት አያዝን?፣
ሲደራረብብኝ ከሀዘን ላይ ሀዘን፣
ቅስሜ እጅግ ቢሰበር ሀዘኔ ባይወጣ፣
እጅጉን ቢጨምር የመከራው ቁጣ፣
ኤሎሄ ኤሎሄ ልበል ለፈጣሪ
ለእውነተኛው ዳኛ፣
ፍፁም ይቅርታውን ፍቅሩን ምህረቱን
እንድሰጠን ለኛ፣
እባክህ አምለኬ ስማኝ ልለምንህ፣
የሞቱትን ምረህ ያሉትን ጠብቀህ፣
እምባችን ታብሶ ደስታ ተተክቶ
ፍቅር እንድመጣ፣
ምህረት ርህራሄ ፍቅር የሞላበት
አድስ ዘመን አምጣ፣
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
(ለሞቱት ወገኖቻችን ነፍሳቸውን በገነት እንድያኖርልን እየተማፀንን ለወዳች ዘመዶቻቸውም መፅናናትን እንመኛለን)
~~~~~~~~~~~~~~~~~~
ሚኪያስ መሰለ
24/01/09 ዓ·ም
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ