21/05/2025
ግንቦት 13/1983 ዓ.ም ጓድ ሊቀመንበር ሲታወሱ፦
====
የዛሬ 34 ዓመት ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ጓድ መንግስቱ ኃይለማርያም ኢትዮጵያን ጥለው የተሰደዱበት ቀን ነው።
ነገሩ እንዲህ ነው።
እለተ ማክሰኛ ግንቦት 13/1983 የፕሬዘዳንቱ ልዩ ረዳት ሻምበል መንግስቱ፥ ብላቴ የጦር ማሰልጠኛ ጣቢያ ደርሶ፥ ከዚያም ወደ አስመራ ደርሶ መልስ የሚበቃ ነዳጅ የሞላ አንድ ዳሽ 5 አውሮፓላን እንዲዘጋጅ ትእዛዝ አስተላለፉ።
በዚያው ዕለት ከጠዋቱ ወደ 2:00 ሰአት ገደማ ፕሬዘዳንቱ በኮ/ል ተስፋዬ መሪነት ከተመረጡ አጃቢዎች እና ከሦስተኛ ክፍለጦር ከተመለመለው አጃቢያቸው ሻምበል ደመቀ ባንጃው ጋር በመሆን ወደ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በማቅናት ተዘጋጅታ ትጠብቅ ከነበረችው አውሮፓላን ተሳፈሩ።
ግንቦት 13 ቀን 1983 ፕሬዘዳንት መንግስቱ የ17 ዓመት ስልጣናቸው ጥለው፥ አብዮታዊት እናት አገራቸውን ለቅቀው ወደ ዚምባብዌ መሰደዳቸውን ከዚያም መፈርጠጣቸውን የኢትዮጵያ ሬዲዮ በተለያዬ ቃና ደጋግሞ አሳወቀን። እኛም በተለያዬ ድራማና ትርክት ስናጣጥመው ኖርን።
እነሆ ክስተቱ ከተስተናገደ 34 ዓመታት ተቆጠሩ።