21/07/2026
የፌደራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን በ2018 በጀት ዓመት ከ9.8 ቢሊዮን ብር በላይ በያዙ መዛግብት ላይ ውሳኔ አሳረፈ፡፡
********************
ፌታይኮ
ሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ
የፌደራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን የኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት፣ ዳኞች፣ የማኔጅመንት አባላት፣ መላው ሠራተኞች እንዲሁም የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን የሥራ ክፍል አመራሮች በተገኙበት የ2018 በጀት ዓመት የይግባኝ አቤቱታዎች፣ የውሳኔ አሰጣጥ ፍጥነትና ጥራት ዝርዝር የአፈጻጸም ሪፖርት ገመገመ።
በበጀት ዓመቱ ለውሳኔ የቀረቡት አጠቃላይ መዛግብት 1,224 ሲሆኑ የያዙት የገንዘብ መጠን 17,676,952,272.95 ብር ሲሆን ከእነዚህም መካከል ከአምናው የዞሩ 469 መዛግብት የያዙት የገንዘብ መጠን 5,229,097,472.14 ብር፣ አዲስ የተከፈቱ 755 መዛግብት የያዙት የገንዘብ መጠን 12,447,854,800.81 ብር ሲሆኑ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የመዛግብት ብዛት በ177 ያነሰ ቢሆንም በገንዘብ መጠን የ5,839,641,152.06 ብር ብልጫ አሳይቷል።
ከቀረቡት 1,224 መዛግብት ውስጥ 960 የሚሆኑትን ክርክር በማድረግ በ958 መዛግብት የያዙት የገንዘብ መጠን 9,864,684,674.39 ብር ላይ ውሳኔ አሳርፏል። በዚህም የውሳኔ አሰጣጥ አፈጻጸም 99.79% ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህ አፈጻጸም ከታቀደው ግብ በ0.21% ዝቅ ያለ ቢሆንም ከባለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ0.33%፣ የ26 መዛግብት እና የ 3,056,471,025.64 ብር ብልጫ አሳይቷል። ቀሪዎቹ 266 መዛግብት መካከል 21 ለመልስ፣ 3 ለብይን ፣ 240 ለቃል ክርክር እና 2 ለውሳኔ ለቀጣይ የተቀጠሩ ናቸው።
እንደ ሕጉ አሰራር ማመልከቻ በደረሰ 120 ቀናት ውስጥ ውሳኔ የሚሰጥ ቢሆንም ውስብስብ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ በፕሬዝደንቱ ፈቃድ እስከ 60 ቀናት ሊራዘም ይችላል። በዚህ መሠረት ውሳኔ ካገኙት 958 መዛግብት ውስጥ 881 መዛግብት (91.96%) በሕጋዊ ገደብ ማለትም በ120 ቀናት እና ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ውሳኔ አግኝተዋል። ከእነዚህም ውስጥ 140 መዛግብት (15%) ከ120 ቀን ባነሰ ጊዜ፣ 741 መዛግብት (77%) ደግሞ በ120 ቀናት ውስጥ የተወሰኑ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 77 መዛግብት (8%) ከ120 ቀናት በላይ ጊዜ የወሰዱ ናቸው።
ውሳኔዎች ከ120 ቀናት በላይ የወሰዱበት ዋና ዋና ምክንያቶች ከሦስተኛ ወገን የሚፈለጉ ማስረጃዎች በወቅቱ አለመቅረብ፣ ከመዝገብ ውስብስብነት የተነሳ ለኮሚሽኑ ፕሬዝደንት ቀርበው የጊዜ ማራዘሚያ በመፈቀዱ እና በተከራካሪ ወገኖች ቀጠሮዎች በተደጋጋሚ በመቀየራቸው ምክንያት መሆኑ ተገምግሟል። በአጠቃላይ የሕግ ተገዢነት ምጣኔ 92% መድረሱ ተረጋገጧል።
ውሳኔ ከተሰጠባቸው መካከል 757 መዛግብት ላይ ለከ/ፍ/ቤት ይግባኝ የተጠየቀ ሲሆን 37 (4.88%) የሚሆኑት በነጥብ ተመልሰዋል። በዚህም መሠረት የጥራት ምጣኔው 95.12% ሆኗል።
ለድጋሚ ምርመራ ከተመለሱት 37 መዛግብት ውስጥ 14 መዛግብት ውሳኔ የሚያስለውጥ አዲስ መረጃ ባለመገኘቱ ሲፀኑ 4 መዛግብት የቀረቡበት አግባብ ታይቶ ሲሻሻል 11 መዛግብት ደግሞ ተሽረዋል (4 በከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ 7 በኮሚሽኑ)። ቀሪዎቹ 8 መዛግብት በአሁኑ ወቅት በመታየት ላይ ይገኛሉ። በዚህ ሂደት የውሳኔዎች የጥራት ምጣኔ ወደ 98.01% ከፍ ለማለት ችሏል።
በበጀት ዓመቱ 342 የአፈጻጸም መዛግብት የቀረቡ ሲሆን 144 መዛግብት ዕግድ፣ 94 መዛግብት ግራ ቀኝ (ሁለቱም ወገኖች) ባለመቅረባቸው ሲዘጉ 31 መዛግብት በውሳኔው መሠረት ሙሉ በሙሉ ሲፈፀሙ 73 መዛግብት በአሁኑ ወቅት በአፈጻጸም ሂደት ላይ ይገኛሉ። ኮሚሽኑ ውሳኔዎችን የማስፈጸም አቅሙን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት የአፈጻጸም መዛግብትን ብቻ ለይቶ የሚያይ የችሎት ቀን መሰየሙ አፈፃፀሙ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰሩ መሆኑ ተገምግሟል፡፡
የምርት ገበያ፣ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አስተዳደራዊ ችሎት እና የፌደራል የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አስተዳደራዊ ይግባኝ ሰሚ ከፍትህ ሚኒስቴር በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት በተገቢው ነፃነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በፌደራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን አስተዳደራዊ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሲሆን በ2018 በጀት ዓመት የምርት ገበያ ህጎች እንዲከበሩ የማድረግ ሚና ቢኖርም በበጀት ዓመቱ የቀረበ አቤቱታ አለመኖሩ የተገመገመ ሲሀን ይሄንንም ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ተደርጓል።
በሌላ በኩል የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አስተዳደራዊ ችሎት በበጀት ዓመቱ 4 አዲስ የፀረ ውድድር መዝገቦች የተከፈቱ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 3ቱ ውሳኔ ሲያገኙ የቀረው 1 መዝገብ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት በቀጠሮ ላይ ይገኛል። በተጨማሪም አንድ ነጋዴ በሌላ ነጋዴ ላይ ባቀረበው አቤቱታ ከባለፈው በጀት ዓመት የዞረ 1 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ግምት ያለው 1 መዝገብ እና 9 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ግምት ያለው 1 አዲስ መዝገብ በድምሩ 10 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ 2 መዝገቦች ቀርበው ሁለቱም እልባት አግኝተዋል። ተገቢ ባልሆነ የንግድ ውድድር ተግባር ምክንያት ለደረሰ ጉዳት ካሳ ይከፈለኝ በሚል የቀረቡ 2 መዝገቦችን ጨምሮ 371 ሺህ 500 ብር በፍትህ ሚኒስቴር አካውንት ገቢ ተደርጓል። ከቀረቡት 5 የአፈፃፀም መዝገቦች ውስጥ 3ቱ ሲፈፀሙ 2ቱ በሂደት ላይ የሚገኙ ሲሆን 8 የብርበራ ትዕዛዝ ይሰጥልኝ አቤቱታዎችም አስተናግዷል። በአጠቃላይ ለችሎቱ የቀረቡ 19 መዛግብት ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ 16ቱ ውሳኔ ሲያገኙ ቀሪዎቹ 3 መዛግብት ወደ ቀጣዩ በጀት ዓመት ተሸጋግረዋል።
የፌደራል የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አስተዳደራዊ ይግባኝ ሰሚ በበኩሉ በስር ዳኝነት ችሎት የተሰጠው ውሳኔ ይሻርልኝ በሚል የቀረቡ 5፣ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር ተፈፅሞብናል በሚል የቀረቡ 3 እንዲሁም የጉዳት ካሳ ይከፈለን በሚል የቀረቡ 2 አቤቱታዎችን ተቀብሎ ያስተናገደ ሲሆን በድምሩ የቀረቡት 5ቱም መዝገቦች ውሳኔ አግኝተዋል። በዚህም ሂደት በ4 መዝገቦች 168 ሺህ 750 ብር የዳኝነት ክፍያ ተሰብስቦ በፍትህ ሚኒስቴር አካውንት ገቢ ሆኗል።
በመጨረሻም መሪ ቃሉን፣ ርዕይ፣ ተልዕኮ እና እሴቶችን በሚገባ ተረድቶ ከራስ ጋር በማዋሃድ እያንዳንዱ የተቋሙ ሠራተኛ ከመንግሥት የተጣለበትን ኃላፊነትና የገባውን ቃል በማክበር ለ2019 በጀት ዓመት የተያዘውን ዕቅድ በስኬት እንዲጠናቀቅ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ የፌደራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት አሳስበዋል፡፡