10/02/2026
በቅ/ፅ/ቤቱ በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 1395/2017 ላይ ስልጠና ተሰጠ
በቦሌ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅ/ጽ/ቤት በተለያዩ ንግድ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ የደረጃ "ሀ" እና የደረጃ "ለ" ግብር ከፋዮች አዲስ በተሻሻለው የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 1395/2017 ላይ ስልጠና ተሰጠ፡፡
ስልጠናው በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የታክስ ከፋዮች ትምህርትና ድጋፍ ቡድን በሆኑት ወ/ሮ የሁሉ ዋሴ አማካኝነት የተሰጠ ሲሆን ስልጠናው የገቢ ግብር አዋጁ ማሻሻል ያስፈለገበት ዋና ዋና ዓላማዎች፣ የግብር ከፋይ ደረጃዎችና አከፋፈል ሁኔታዎች፣ ስለ አማራጭ አነስተኛ ግብር አከፋፈል፣ ለበጎ አድራጎት ዓላማ የሚደረጉ ስጦታዎች፣ የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ስላለባቸው ግብር ከፋዮች ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
እንዲሁም የጥሬ ገንዘብ ክፍያ አፈጻጸም ዘዴዎች፣ ከመቀጠር የሚገኝ ገቢ ግብር ምጣኔዎች፣ የኪራይ ገቢ ግብር ምጣኔዎች፣ በንግድ ሥራ ገቢ ላይ ተፈጻሚ የሚሆኑ ምጣኔዎች፣ ሌሎች (ሠንጠረዥ “መ” ) ገቢዎች፣ ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ግብር ቀንሶ ስለማስቀረት እና ከዲጂታል ይዘት ፈጠራ የሚገኝ ገቢ በሚሉ ዋና ዋና ርዕሶች ላይም ስልጠናው ተሰጥቷል።
በመድረኩም ከሠልጣኞች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን ለተነሱት ጥያቄዎችም የቅ/ፅ/ቤቱ የታክስ ከፋዮች ትምህርት ድጋፍ እና የህግ ተገዥነት ስጋት ስራ አመራር የስራ ሂደት በሆኑት በአቶ መላኩ ደርሶ እና የታክስ ከፋዮች ትምህርትና ድጋፍ ቡድን በሆኑት ወ/ሮ የሁሉ ዋሴ ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥተዋል።