ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ - Freedom and Equality Party

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ - Freedom and Equality Party ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ
ሚዛናዊ እና ምክንያታዊ ፖለቲካ

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ሂደት እና ውጤት ግምገማ እና ምክረ ሀሳቦች።  ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የ7ኛ ጠቅላላ...
29/06/2026

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
የ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ሂደት እና ውጤት ግምገማ እና ምክረ ሀሳቦች።


ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ውጤት መገለጽን ተከትሎ በምርጫው ሂደት እና ውጤት ዙሪያ ሰፊ እና ጥልቅ ግምገማ አድርጓል። ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከፓርቲው ብሄራዊ ምርጫ አስተባባሪ ኮሚቴ የቀረበለትን የምርጫ እቅድ ክንውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ እና ድህረ ምርጫ የተሰሩ ስራዎችን፣ ያጋጠሙ ችግሮችን፣ የተገኙ ውጤቶችን እና ተሞክሮዎችን በመገምገም ለቀጣይ የፓርቲው የምርጫ ተሳትፎ ውጤታማነት እና ለሀገራችን የምርጫ ስርዓት መሻሻል ይበጃሉ ያላቸውን ምክረ ሀሳቦች አስቀምጧል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ባዘጋጀው “የምርጫ ስትራቴጂ” እየተመራ በቅድመ ምርጫ ወቅት ውጤታማ ስራዎችን አከናውኗል። በዚህ ምዕራፍ ከተሰሩ ስራዎች ውስጥ ልዩ ልዩ የምርጫ ማስፈጸሚያ መመሪያዎች እና የአሰራር ደንቦች ማዘጋጀት፣ የእጩዎች ምልመላ እና ምዝገባ፣ የምርጫ ክርክር፣ የነጻ ሰዓት መልእክቶች ዝግጅት እና ስርጭት፣ የመራጮች ምዝገባ ቅስቀሳ እና ክትትል፣ የፓርቲ ወኪል ታዛቢዎች ምልመላና እና ስምሪት፣ የጎዳና ላይ፣ የቤት ለቤት እና የአዳራሽ ውስጥ የምርጫ ቅስቀሳዎች ይገኙበታል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ካደረጋቸው ዝግጅቶች መካከል አንዱ እና ዋነኛው በመረጃ ላይ የተመሰረተ የምርጫ ማንፌስቶ ማዘጋጀት ሲሆን፣ በምርጫ ክርክር መድረኮች፣ በምርጫ ቅስቀሳ እና በሌሎች አጋጣሚዎች ለህዝብ እንዲደርስ አድርገናል። ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ጥምረት ለመፍጠር አስፈላጊ ዝግጅት እና ከነእፓ ጋር ተቀራራቢ አጀንዳ ሊኖራቸው ይችላል ተብሎ ከታመነባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ሰፊ ውይይት ማድረግ በቅድመ ምርጫ ከተሰሩ ስራዎች ውስጥ ይገኛል። ለምርጫ የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ሀብት ከአባላት እና ከደጋፊዎች ለማሰባሰብ ሰፊ ስራዎች ተከናውነዋል።

እነዚህ እና ሌሎች በርካታ ቅድመ ምርጫ ስራዎች ነእፓ በዜጎች ዘንድ በስፋት እንዲታወቅ እና ሰፊ ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርገዋል። የነእፓ አማራጭ የፖሊሲ አማራጮች ከፓርቲው ሚዛናዊ እና ምክንያታዊ ፖለቲካ መርሆች ጋር ተዋህደው፣ ፓርቲያችን በመላ የሀገራችን አካባቢዎች እጅግ ሰፊ የህዝብ ተቀባይነት እና ድጋፍ እንዲያገኝ አድርጎታል። በቅድመ ምርጫ ወቅት የፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች ባደረጉት የተቀናጀ እና መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ነእፓ የዜጎችን ቀልብ መግዛት እንዲችል፣ የፓርቲው የምርጫ ምልክት የሆነው ብዕር በዜጎች ልብ ውስጥ ታትሞ እንዲቀመጥ አድርጓል። በዚህም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነእፓ ታሪካዊ ድል ተጎናጽፏል።

ውድ የነእፓ አባላት፣ ደጋፊዎች እና መላ የሀገራችን ህዝቦች
ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ የተሻለ ዝግጅት እና ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲሁም ከፍተኛ የህዝብ ቅቡልነት ማግኘት ቢችልም፣ በምርጫው ሂደት ላይ በተስተዋሉ የምርጫ ህግን እና አሰራርን የሚጥሱ ተግባራት ምክንያት የሚገባውን ውጤት ማግኘት ሳይችል ቀርቷል። ፓርቲው በተለያየ ደረጃ ባዋቀራቸው የምርጫ ክትትል ዴስኮች ከተመዘገቡ ቅድመ ምርጫ እና ምርጫ ችግሮች መካከል፣

📍በተለያየ እርከን ላይ የሚገኙ የመንግስት ሹመኞች እና የገዢ ፓርቲ አመራሮች በመራጩ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ጫና ማድረግ፣ ከምርጫ ቀን አስቀድሞ የመንግስት አካላት ቤት ለቤት በመሄድ ዜጎች ገዢውን ፓርቲ እንዲመርጡ ማስፈራራት እና የስነ ልቦና ጫና ማድረግ፣ የፓርቲው እጩዎች ከእጩነት እንዲወጡ ከፍተኛ ግፊት ማድረግ፣ የመንግስት እና የህዝብ ሀብትን ለምርጫ ስራ በስፋት መጠቀም፣

📍በምርጫው እለት በበርካታ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ድምጽ ለመስጠት የተሰበሰው ህዝብ ገዢውን ፓርቲ እንዲመርጥ መወትወት፣ ከዚህ አልፎ በሚስጥር ድምጽ በሚሰጥበት ቦታ በመግባት መራጩ ህዝብ ማንን መምረጥ እንዳለበት ማስገደድ፣ የድምጽ መስጫ ሰዓት መራዘምን ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች የምርጫ ህግን እና አሰራርን የሚጥሱ ተግባራት መፈጸም፣

📍የምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኛ አለመሆን፣ በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች አንዳንድ ኃላፊነት የጎደላቸው ምርጫ አስፈጻሚዎች ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር ድምጽ ያልተሰጠባቸው የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ድምጽ የመስጠት ህገ ወጥ ተግባር ላይ መሳተፍ፣

📍በድምጽ ቆጠራ ወቅት ፍጹም ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ፓርቲያችን ያገኘውን ድምጽ ለሌሎች ፓርቲዎች በመስጠት ፓርቲያችን ሊያገኝ ይችል የነበረው ውጤት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ማድረግ። በተመሳሳይ በአንዳንድ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ለፓርቲያችን የተሰጡ ድምጾች እንዲባክኑ በድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ተጨማሪ ምልክቶች ማስቀመጥ፣

📍በተለያዩ ክልሎች ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ፍቃድ የተሰጣቸው የነእፓ ወኪል ታዛቢዎች ምርጫውን መታዘብ እንዳይችሉ ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዳይገቡ በማድረግ ምርጫው ያለ ነእፓ ታዛቢዎች እንዲካሄድ ማድረግ። ከድምጽ መስጫ ቀን በኃላ ባሉ ተከታታይ የድምጽ ቆጠራ እና በምርጫ ክልል ጽ/ቤቶች በተደረጉ የድምጽ ማዳመር ስራዎች የፓርቲያችን ታዛቢዎች እንዳይሳተፉ መከልከል፣

📍በ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ የነእፓን ጨምሮ የሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ውጤት ዝቅተኛ እንዲሆን ካደረጉ በርካታ ምክንያቶች መካከል የፓርቲዎች በትብብር አለመስራት አንዱ ነው። ፓርቲዎች በምርጫው የነበራቸው የተናጠል ተሳትፎ ድምጽ እንዲከፋፈል አድርጓል። ነእፓ ከምርጫው አስቀድሞ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በትብብር እጩ የማቅረብ ሀሳብ አቅርቦ ለተግባራዊነቱ ሰፊ እንቅስቃሴ ቢያደርግም ሊሳካ አለመቻል፣

📍በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች በተለይም በተወሰኑ የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው የጸጥታ መደፍረስ በነእፓ የምርጫ እንቅስቃሴ እንዲሁም በምርጫው አጠቃላይ ሂደት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደር። በዚህም ምክንያት በእነዚህ አካባቢዎች በቂ እጩዎችን ማቅረብ፣ የጎዳናም ሆነ የቤት ለቤት የምርጫ ቅስቀሳ ማካሄድ ያልተቻለ ሲሆን ይህም በፓርቲው የምርጫ ውጤት ላይ ተጽእኖ አሳድሯል። ከዚህ ባሻገር በአካባቢዎቹ ያለውን የጸጥታ መደፍረስ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም አንዳንድ ኃይሎች በምርጫ ሂደት ህገወጥ ተግባር ውስጥ መሳተፍ።

በጠቅላላው በድምጽ አሰጣጥ፣ በድምጽ ቆጠራ እና ድምጽ ማዳመር ወቅት በአንዳንድ የምርጫ ክልሎች የምርጫውን ውጤት በጉልህ ሊቀይሩ የሚችሉ የአሰራር ግድፈቶች መፈጸማቸውን መገንዘብ ተችሏል። በምርጫ ሂደት የተፈጸሙ የህግ ጥሰቶችን የሚያሳዩ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ፣ የተፈጸሙት የህግ ጥሰቶች በህግ አግባብ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አቤቱታ አቅርበናል።


በቅድመ ምርጫ እና በምርጫ ወቅት የተከሰቱ እነዚህ እና ሌሎች በርካታ ችግሮችን አልፈን በኢ.ፊ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በተለያዩ የክልል መስተዳድር ምክር ቤቶች የተወሰኑ መቀመጫዎችን ማግኘት ችለናል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የተጠቃለለ የምርጫ ውጤት መሰረት ነእፓ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3 መቀመጫ እንዲሁም በሰባት ክልል መስተዳድር ምክር ቤቶች 35 መቀመጫዎች አግኝቷል። ነእፓ ካገኛቸው እነዚህ ወንበሮች በብዙ እጥፍ የሚበልጡ እና የባከኑ ከፍተኛ የህዝብ ድምጽ ማግኘቱን ልብ ይሏል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ባለፉት አምስት ዓመታት ባከናወናቸው ሰፊ ድርጅታዊ እና የአቅም ግንባታ ስራዎች እንዲሁም በምርጫ ወቅት ባካሄዳቸው የምርጫ እንቅስቃሴዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት አስመዝግቧል ማለት ይቻላል። በተለያዩ ችግሮች ውስጥ አልፈን፣ በምርጫው ያገኘናቸው ውጤቶች እና ያሳካናቸው ግቦች ነእፓ በቀጣይ በሚኖረው የምርጫ ተሳትፎ እና የፖለቲካ እንቅስቃሴ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችል ትልቅ ግብአት ይሆናሉ ብለን እናምናለን።


የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የፓርቲያችንን የ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ እንቅስቃሴ እና ውጤት በጥልቀት ከገመገመ በኃላ የፓርቲያችንን ቀጣይ የምርጫ ተሳትፎ ውጤታማነት እንዲሁም የሀገራችንን የምርጫ ስርዓት፣ ሂደት እና ውጤታማነት ለማሻሻል ይረዳሉ ያላቸውን የሚከተሉትን ምክረ ሀሳቦች እና የስራ አቅጣጫዎች አስቀምጧል፣

1. ፡ የምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኛ አለመሆን እና የብቃት ማነስ በምርጫው ሂደት እና ውጤት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ገለልተኛ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ፣ ምደባን እና ብቃት በተመለከተ ነእፓ ዓለም አቀፍ ተሞክሮን ያገናዘበ ጥናት በማካሄድ ግኝቶቹን ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እንዲያቀርብ፣

2. ፡ የምርጫ ታዛቢዎች ገለልተኛነት ለአንድ ምርጫ ነጻ እና ፍትሀዊ መሆን ከፍተኛ ድርሻ አለው። የምርጫ ታዛቢዎች በድምጽ አሰጣጥ እና ድምጽ ቆጠራ ሂደት የዜጎች ድምጽ እንዲከበር ትልቅ ሚና አላቸው። ይሁን እንጂ በሀገራችን “በገለልተኛ ታዛቢ” ስም በምርጫ የሚሳተፉ የምርጫ ታዛቢዎች የገለልተኛ ታዛቢነት መርህን ፍጹም በሚጻረር ሁኔታ የአንድ ወገን ደጋፊ ሆነው ሲያገለግሉ ይስተዋላል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ የታዛቢዎች ምልመላ እና ምደባ በተመለከተ በስራ ላይ ያሉ የህግ ማእቀፎች እና አሰራሮች እንዲሻሻሉ ነእፓ የራሱን ጥናት በማድረግ ለሚመለከታቸው አካላት ምክረ ሀሳብ እንዲያቀርብ፣

3. ፣ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በመደበኛ ጊዜ እንዲጠናቀቅ ማድረግ፡ በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች የድምጽ አሰጣጥ ሂደት እጅግ አዝጋሚ መሆን፣ ዜጎች ድምጻቸውን ለመስጠት ለረዥም ሰዓት ተሰልፈው እንዲጠብቁ አድርጓል። አዝጋሚ የሆነው የድምጽ አሰጣት ሂደት የድምጽ መስጫ ሰዓት እንዲራዘም ያደረገ ሲሆን፣ ይህም በተያያዥ የድምጽ ቆጠራ ስራ በወቅቱ እንዳይጀመር አድርጓል።

ከመደበኛ የድምጽ መስጫ ሰዓት ውጪ የሚካሄድ የድምጽ አሰጣጥ እና የድምጽ ቆጠራ ሂደት ምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የፓርቲ ወኪሎች እና ሌሎች “ገለልተኛ ታዛቢዎች” በድካም ስሜት ስራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ ያደረገ ሲሆን፣ ለብልሹ አሰራር ምቹ እድል ፈጥሯል። ይህንን ችግር ለመፍታት የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ በመደበኛ ሰዓት እንዲጠናቀቅ እና የድምጽ ቆጠራው በወቅቱ ተጀምሮ መጠናቀቅ የሚችልበት የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፣

4. ፡ በእያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ እና ምርጫ ክልል ጽ/ቤቶች የፓርቲ ወኪሎች (ታዛቢዎች) መገኘት ፓርቲው የሚያገኘውን ድምጽ ለመጠበቅ እና ህገ ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጾ አለው። በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በነበረብን ከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች በቂ የፓርቲ ወኪሎችን መመደብ አለመቻላችን ፓርቲው ያገኘውን ከፍተኛ የህዝብ ድምጽ ከህገ ወጥ ተግባራት መጠበቅ እንዳይችል ያደረገ ሲሆን፣ ይህም ፓርቲው ባገኘው ውጤት ላይ እጅግ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል።

በመሆኑም በቀጣይ በሚካሄዱ ምርጫዎች በእያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ እና ምርጫ ክልል ጽ/ቤቶች በቂ ተቀማጭ እና ተንቀሳቃሽ የፓርቲ ወኪሎች ለማስቀመጥ በቂ ሀብት እንዲመደብ እና ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ፣

5. ፡ የፓርቲውን የምርጫ እንቅስቃሴ በጉልህ እንዲገደብ ካደረጉ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ እና ዋነኛው የፋይናንስ እጥረት ነው። የፋይናንስ እጥረት የፓርቲው የምርጫ ቅስቀሳ በከፍተኛ ደረጃ እንዲወሰን፣ በቂ እጩዎችን እና ታዛቢዎችን ማቅረብ እንዳይቻል እና ሌሎች ወሳኝ ስራዎች በተያዘላቸው ጥራት እና ብዛት እንዳይሰሩ አድርጓል። በመሆኑም በቀጣይ ፓርቲው በሚሳተፍባቸው ምርጫዎች በቂ ሀብት ለማንቀሳቀስ ልዩ ስራ እንዲሰራ፣

6. ፡ ነእፓ በ6ኛው እና በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫዎች ያገኘው ከፍተኛ የመራጭ ድምጽ እንዲባክን እንዲሁም የሀገራችን ጠቅላላ የምርጫ ሂደት እና ውጤት ፍትሀዊ እንዳይሆን ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ኢ ፍትሀዊ የሆነው የምርጫ ስርዓታችን ነው። በመሆኑም ይህ ኢፍትሀዊ የምርጫ ስርዓት ይቀየር ዘንድ በቀጣይ በሀገራችን በሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በትብብር እንዲሰራ፣

7. ፡ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፓርቲው የተሻለ ውጤት ያገኘባቸው አካባቢዎች፣ የተሻለ አደረጃጀት እና የተሻለ አመራር ያለባቸው አካባቢዎች እንደሆኑ ለመረዳት ተችሏል። የተሻለ የምርጫ ውጤት፣ ሰፊ እና ተከታታይ የአደረጃጀት ስራ የሚሻ ተግባር ነው። በመሆኑም ከምርጫ ማግስት ጀምሮ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የፓርቲውን ነባር አደረጃጀት ይበልጥ ለማጠናከር እና አደረጃጀት ባልተዘረጋባቸው አካባቢዎች የፓርቲውን መዋቅር ለመዘርጋት ሰፊ የአባላት ምልመላ እና አደረጃጀት ስራ እንዲሰራ፣

8. ፡ የሀገር ሰላም እና የዜጎች ደህንነት በሀገራችን ነጻ፣ ፍትሀዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ እጅግ አስፈላጊ ነው። በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የቀጠለው የሰላም መደፍረስ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እንቅስቃሴአችን ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ አሳድሯል። በመሆኑም ነእፓ ሁሌም ለሰላም መስፈን የሚያደርገውን ጥረት በቀጣይ አጠንክሮ በመቀጠል፣ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም ይሰፍን ዘንድ የድርሻውን መወጣት የሚያስችለው ስራዎችን መስራት። ከዚህ አንጻር ቀደም ሲል ነእፓ የጀመረው “ኢትዮጵያ በልጆቿ ትታረቅ” የሰላም ግንባታ ፕሮጀክት ተግባራዊ መሆን የሚችልበትን ሌላ እድል መሞከር፣

9. ፡ 7ኛ ጠቅላላ ምርጫን ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀው የፓርቲው የመጀመሪያ የሶስት ዓመት (2016-2018) ስትራቴጂክ እቅድ ከ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ጋር ተጠናቋል። በመሆኑም 2ኛው የፓርቲው ስትራቴጂክ እቅድ (2019- 2023) 8ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ታሳቢ አድርጎ እንዲዘጋጅ፣

10. ፡ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሁሉም ደረጃ ያደረገው እንቅስቃሴ፣ መልካም ተሞክሮዎች፣ ተግዳሮቶች፣ በዝርዝር ተጠንተው ለቀጣይ ምርጫ ትምህርት በሚሰጥ መልኩ ተሰንደው እንዲቀመጡ፤ እንዲሁም የሀገራችንን የምርጫ ስርዓት እና አሰራር እንዲሁም የሀገራችንን የፖለቲካ ምህዳር ለማዘመን ልዩ ልዩ የህግ እና የስርዓት ማሻሻያ ጥናቶች እንዲካሄዱ እና የጥናቶቹ ግኝቶች ለፖሊሲ አውጪ አካላት በግብአትነት እንዲቀርቡ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል።



#ምስጋና፡ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ልዩ ልዩ አስተዋጾ ላበረከቱ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ከፍተኛ ምስጋና እናቀርባለን። ከሁሉም በማስቀደም ውስብስበ አሰራር፣ ሰፊ የሎጂስቲክስ፣ ጠንካራ የስራ እና የፋይናንስ እቅድ እና ዲሲፕሊን የሚሻውን ጠቅላላ ምርጫ እንዲሳካ፣ ነእፓን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሂደት ያጋጠሟቸው ችግሮች እንዲፈቱ ከፍተኛ ድጋፍ ላደረጉ የምርጫ ቦርድ ስራ አመራር አባላት እና ሰራተኞች ከፍ ያለ ምስጋና እናቀርባለን።

በተለያዩ ክልሎች እና ከተማዎች ምርጫ ቅስቀሳ በምናካሂድበት ወቅት ልዩ ልዩ ድጋፍ ላደረጉልን የክልል እና የከተማ መስተዳድሮች፣ የጸጥታ አካላት፣ ለምርጫው ማስፈጻሚያ የፋይናንስ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ላደረጉ የፓርቲያችን አባላት እና ደጋፊዎች፣ በምርጫ ክርክር እና በነጻ የአየር ሰዓት አጠቃቀም ወቅት ድጋፍ ላደረጉልን የሚዲያ ተቋማት እና ሌሎች በምርጫ ሂደት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ድጋፍ ላደረጉልን አካላት ላቅ ምስጋና እናቀርባለን። የሀገር ባለቤትነቱን በድምጹ ለማረጋገጥ ረዢም ሰዓት ተሰልፎ ድምጻቸውን ለሰጡ ኢትዮጵያውያን ያለንን ከፍተኛ አድናቆት እና ምስጋና እንገልጻለን።


ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህዝብ ድጋፍ አግኝተው ለመመረጥ ከፍተኛ ፉክክር የሚያደርጉበት የፖለቲካ ሂደት ሲሆን፣ በምርጫ ማግስት የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ እና እድገቷን ለማስቀጠል ከፉክክር ይልቅ በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑን ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ይገነዘባል። በመሆኑም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መጠናቀቁን እና የምርጫው ውጤት ይፋ መሆኑን ተከትሎ ፓርቲያችን ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከመንግስት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በሁሉም መስክ በትብብር ይሰራል።

ፉክክርን እና ትብብርን በሚዛን ጠብቆ ድርጅታዊ እና ሀገራዊ ተግባር እና ኃላፊነትን መወጣት የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የሚዛናዊ ፖለቲካ አንዱ መገለጫ ነው። ነእፓ የሚከተለው ሚዛናዊ የትብብር እና ፉክክር መርህ በተለይ ሀገራችን በተለያዩ ውስጣዊ ፈተናዎች እና የውጭ ጫናዎች ውስጥ እያለፈች በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት እጅግ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን።

በዚሁ መሰረት የሀገራን ሰላም በማስጠበቅ፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ ብሄራዊ ጥቅምን በማስከበር እና ሌሎች ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንሰራለን። በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የፓርቲው መዋቅሮች ብሄራዊ ምክክርን ጨምሮ በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በትብብር ይሰራሉ።

ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ውይይቱን ሲያጠናቅቅ በምርጫው አብላጫ ድምጽ ያገኘው ብልጽግና ፓርቲ በሀገራችን ጠንካራ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ለመገንባት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በትብብር እንዲሰራ፣ በተመሳሳይ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በክልል ምክር ቤቶች ድምጽ ያገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰጣቸውን የህዝብ ውክልና በኃላፊነት እና በተጠያቂነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጥሪ አስተላልፏል።

በመጨረሻም ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በተለያዩ የክልል መስተዳድር ምክር ቤቶች ያገኛቸውን ወንበሮች በመጠቀም በሀገራችን ሰላም፣ ልማት እና መልካም አስተዳደር እውን ይሆኑ ዘንድ ለዜጎች የገባነውን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ፣ አስፈላጊውን ሁሉ የሚያደርግ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ በድጋሜ እያረጋገጥን፣ መጪው ጊዜ በሀገራችን አስተማማኝ ሰላም፣ ልማት እና ሀገራዊ መግባባት የሚረጋገጥበት ዘመን ይሆን ዘንድ ምኞታችንን እንገልጻለን።

!!

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ
ብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
ሰኔ፣ 2018

29/06/2026

ከቆይታ በኃላ
የነእፓ ብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ሂደት እና ውጤት ግምገማ። ብዕር አሸንፏል!!

7ኛ ጠቅላላ ምርጫ የክልል ምክር ቤቶች የምርጫ ውጤት********************************************የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት በዛሬ እ...
21/06/2026

7ኛ ጠቅላላ ምርጫ የክልል ምክር ቤቶች የምርጫ ውጤት
********************************************
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤት በዛሬ እለት ይፋ አድርጓል። በዚሁ መሰረት በምርጫ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየክልሉ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤቶች ያሸነፉት ወንበር ብዛት ታውቋል።

ቦርዱ ባቀረበው ውጤት የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በሰባት ክልሎች በድምሩ 35 መቀመጫዎችን አሸንፏል። ነእፓ ዛሬ ይፋ በሆነው የምርጫ ውጤት በየክልሉ ያገኘው መቀመጫዎች ብዛት ዝርዝር አባሪ በተደረገው ሰንጠረዥ ቀርቧል።

በተለያዩ ክልሎች ምክር ቤቶች ላሸነፉ የፓርቲያችን አባላት መልካም የስራ ጊዜ እንመኛለን።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ
ሰኔ 14፣ 2018

እንኳን ደስ አለን!! ጉዞ ወደ ፓርላማ!! የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ትላንት ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት ሪፖርት ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለህዝብ ተወካዮ...
18/06/2026

እንኳን ደስ አለን!!
ጉዞ ወደ ፓርላማ!!

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ትላንት ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት ሪፖርት ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካቀረባቸው እጩዎች መካከል ሶስቱ ማሸነፋቸውን አሳውቋል።

ነእፓ ፓርቲያችንን እና ያቀረባቸውን እጩዎች ተቀብሎ በየምርጫ ክልሎቹ ድምጹን ለሰጠን ህዝብ እጅግ ላቅ ያለ ምስጋና ያቀርባል።

ተመራጭ የህዝብ እንደራሴዎቻችን የመረጣቸውን ማህበረሰብ እና መላ የሀገራችንን ህዝቦች በቅንነት፣ በታማኝነት እና በቁርጠኝነት እንደሚያገለግሉ ነእፓ ያረጋግጣል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች የህዝብ ተወካዮቹ አማካኝነት በሀገራችን ሰላም እንዲረጋገጥ፣ ልማት እውን እንዲሆን፣ የዜጎች መሰረታዊ ፍላጎቶች እንዲሟሉ፣ ዜጎች በቂ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ማግኘት እንዲችሉ ይሰራል። የዜጎች የነጻነት፣ የእኩልነት እና የፍትህ ድምጽ እንዲሰማ አጥብቆ ይታገላል።

የሌሎች የፓርቲያችን ተወዳዳሪዎች ውጤት በቦርዱ ይፋ ሲደረግ እናሳውቃለን።

ለፓርቲያችን ተወካዮች መልካም የስራ ዘመን እንመኛለን!!

ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትህ!!
ሰኔ 11 2018

የነእፓ ሊቀመንበር ዶ/ር አብዱልቃድር አደም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መጠናቀቅን ተከትሎ ያስተላለፉት መልእክት።የተከበራችሁ የነእፓ ብሄራዊ ምክር ቤት አባላት የተከበራችሁ የነእፓ ስራ አስፈጻሚ ኮ...
03/06/2026

የነእፓ ሊቀመንበር ዶ/ር አብዱልቃድር አደም 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ መጠናቀቅን ተከትሎ ያስተላለፉት መልእክት።

የተከበራችሁ የነእፓ ብሄራዊ ምክር ቤት አባላት
የተከበራችሁ የነእፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት
የተከበራችሁ የብሄራዊ፣ የክልል እና የዞን ምርጫ አስተባባሪ ኮሚቴዎች አባላት
የተከበራችሁ የነእፓ አባላት፣ ደጋፊዎች እና መላ የሀገራችን ህዝቦች

በቅድሚያ እጅግ የከበረ ሰላምታየ በያላችሁበት ይድረሳችሁ

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤታማ ለመሆን ላለፉት ጥቂት ወራት በከፍተኛ ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት ጊዜያችሁን፣ ጉልበታችሁን፣ ገንዘባችሁን፣ እውቀታችሁን ሳትሰስቱ ለምርጫ ስራ በማዋል ታሪካዊ ኃላፊነታችሁን ተወጥታችኋል። የፖለቲካ ትግል ከፍተኛ መስወአትነት የሚጠይቅ፣ ፍሬው ረዢም ጊዜ እና ትእግስት የሚሻ ስራ እና ኃላፊነት ነው። ከሰራነው ስራ እና ከድካማችን አንጻር የምንጠብቀው ውጤት ትንሽ ሊዘገይ ይችል ይሆናል። ውጤት መምጣቱ ግን አይቀሬ ነው።

ባለፉት በርካታ አመታት እንደ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በጋራ አላማ ዙሪያ ተሰባስበን፣ በአንድ ሀገር ልጅነት እጅ ለእጅ ተያይዘን በሚዛናዊነት እና ምክንያታዊነት የትግል ስልት የሰለጠነ ፖለቲካ አካሂደናል። በዚህም በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ ትንሽም ብትሆን በጎ አበርክቶ አስቀምጠናል ብለን እናምናለን።

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ እጅግ በርካታ ስራዎችን እየተመካከርን እና እየተጋገዝን ሰርተናል። ለሀገራችን ህዝቦች በየዘርፉ አማራጭ ፖሊሲዎችን አቅርበናል። ሚዛናዊ እና ምክንያታዊ ፖለቲካን በተግባር አሳይተናል። በእርግጠኝነት የዚህ ስራችን ውጤት ለፓርቲያችን ብሎም ለሀገራችን እና ለህዝባችን ያለውን ከፍተኛ ፋይዳ በቅርብ ጊዜ ውስጥ እናያለን።

በ7ኛ ጠቅላላ ምርጫ በተለያዩ ክልሎች የክልል ምክር ቤት እንዲሁም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይብዛም ይነስም ወንበሮችን እንደምናሸንፍ እንጠብቃለን። የምርጫውን የተጠቃለለ ውጤት በሚቀጥሉት ቀናት የምናውቅ ይሆናል። በዚህ ምርጫ ከምናሸንፈው የወንበር ቁጥር ባልተናነሰ ምርጫን የማስተዳደር እና የመምራት ከፍተኛ ልምድ አግኝተናል።

በዚህ ምርጫ ያገኘነው ተሞክሮ እና ልምድ በ6ኛ ጠቅላላ ምርጫ ካገኘነው ልምድ ጋር ተዳምሮ ፓርቲያችን በቀጣይ ምርጫዎች የተሻለ ውጤታማ እንዲሆን ትልቅ ፋይዳ አለው ብየ አምናለሁ። በምርጫ የነበረንን ተሳትፎ፣ ጠንካራ ጎኖች እና ውስንነቶች በሚገባ አጠናቅረን ለቀጣይ የምርጫ ተሳትፎአችን ግብአት እንዲሆነን ሰንደን እናስቀምጣለ።

ውድ የነእፓ አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች

ፓርቲያችን በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤታማ ይሆን ዘንድ ላደረጋችሁት ከፍተኛ መስዋአትነት እና ለከፈላችሁት ዋጋ በብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስም የላቀ ምስጋና አቀርባለሁ። በተመሳሳይ ነእፓን ወክለው በምርጫ ለተሳተፉ እጩዎቻችን፣ ለምርጫ ስራችን ድጋፍ ላደረጉልን የነእፓ አባላት እና ደጋፊዎች፣ በምርጫው እለት በምርጫ ጣቢያዎች እና ምርጫ ክልሎች ለተሳተፉ የፓርቲ ወኪሎቻችን፣ በምርጫው ድምጻቸውን ለሰጡን ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ድምጻቸውን ላልሰጡን፣ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ድጋፍ ላደረጉን የጸጥታ አካላት እና የመንግስት ተቋማት እንዲሁም ሌሎች በተለያየ መንገድ ድጋፋቸውን ለሰጡን ሁሉ ልባዊ ምስጋና አቀርባለሁ።

7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ባገባደድንበት እለት ማግስት ወደ ቀጣይ ምዕራፍ፣ ወደ ቀጣይ ትግል እና ቀጣይ ስራዎች ለመሸጋገር ራሳችንን እንድናዘጋጅ ላስታውሳችሁ እወዳለሁ። ትግላችን በሀገራችን ነጻነት፣ እኩልነት እና ፍህት እስኪረጋገጥ ይቀጥላል።

ከአክብሮት ሰላምታ ጋር
አብዱልቃድር አደም
ሊቀመንበር

ግንቦት 25፣ 2018

የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ስራ አስፈፃሚና ህግ ጉዳይ ዘርፍ ሀላፊ ጠበቃ አዲስ መሀመድ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።ለጠበቃ አዲስና በምርጫ ክልሉ ለሚወዳደሩ የነእፓ እጩዎች...
01/06/2026

የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ስራ አስፈፃሚና ህግ ጉዳይ ዘርፍ ሀላፊ ጠበቃ አዲስ መሀመድ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

ለጠበቃ አዲስና በምርጫ ክልሉ ለሚወዳደሩ የነእፓ እጩዎች መልካም እድል እንመኛለን።

በኢፌድሪ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታና የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ወ/ሮ ነቢሀ መሀመድ አብድልሀኪም በሀላባ ምርጫ ክልል ቁጥር አንድ በሸኖ ጣቢያ በመገኘት...
01/06/2026

በኢፌድሪ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታና የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ወ/ሮ ነቢሀ መሀመድ አብድልሀኪም በሀላባ ምርጫ ክልል ቁጥር አንድ በሸኖ ጣቢያ በመገኘት ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

01/06/2026

ጠንካራ ፓርቲ!! ጠንካራ መንግስት!!
ጠንካራ ሀገር!!

01/06/2026

አንድ ድምጽ ልዩነት ያመጣል!!
በየትኛውም ሁኔታ ድምጽዎን ለነእፓ ይስጡ!!

የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ዘኑር አብዱልወሀብ በቅበት ምርጫ ክልል ሻድገር አምቢቾ ምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፅ ሰጡለአቶ ዘኑር እና በክልሉ ለሚወዳደሩ የነእፓ እጩ ተ...
01/06/2026

የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ዘኑር አብዱልወሀብ በቅበት ምርጫ ክልል ሻድገር አምቢቾ ምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፅ ሰጡ

ለአቶ ዘኑር እና በክልሉ ለሚወዳደሩ የነእፓ እጩ ተወዳዳሪዎች መልካም እድል እንመኛለን

Address

Adot Building
Addis Ababa

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ - Freedom and Equality Party posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Organization

Send a message to ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ - Freedom and Equality Party:

Shortcuts

Share