09/04/2026
በዲጂታል ዘመን የእጅ ስልክዎ የባንክ ሂሳብዎ መሆኑን ያውቃሉን⁉️
+++++++++++++++
ባንበት በዚህ ዘመን የዲጂታል አገልግሎቶች እንደ ሀገር እያደገ ይገኛል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የዲጂታል ማጭበርበርን ለመከላከል የሚያስችሉ የጥንቃቄ መልዕክት ሲተላለፉም ይሰተዋላል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባወጣው መረጃ እንዳመላከተው በዲጂታል ዘመን ስልክ እንደ ባንክ ሂሳብ እያገለገለ መሆኑን ጠቅሶ፣ ደንበኞች በጥቃቅን ስህተቶች የዘመናት ጥሪታቸውን ለዘራፊዎች አሳልፈው እንዳይሰጡ አሳስቧል።
ሚስጥራዊ ቁጥሮችን ለሌላ አካል አሳልፎ መስጠት ለማጭበርበር ዋነኛው መንገድ እየሆነ መጥቷል ብሏል።
ደንበኞች ሊተገብሯቸው የሚገቡ ስድስት ቁልፍ ነጥቦችን እንደሚከተለው ዘርዝሯል፤
• ሚስጥራዊነትን መጠበቅ፦ ማንኛውም ደንበኝ የባንክ ሂሳብ ቁጥሩን፣ የሞባይል ባንኪንግ የይለፍ ቃልና በስልክ የሚላኩ የአንድ ጊዜ የማረጋገጫ ቁጥሮችን (OTP) ለማንኛውም አካል አሳልፎ መስጠት የለበትም።
• አጠራጣሪ ጥሪዎች፦ ባንኩ በስልክ ደውሎ ሚስጥራዊ ቁጥር እንደማይጠይቅ ያስታወሰው መግለጫው፣ ደንበኞች በማይታወቁ አካላት የሚላኩ ሊንኮችን እንዳይከፍቱ አስጠንቅቋል።
• የይለፍ ቃል ጥንካሬ፦ የሞባይል ባንኪንግ የይለፍ ቃል ቢያንስ ስድስት ድጂትና በቀላሉ የማይገመት መሆን እንዳለበት ተመልክቷል።
• የማህበራዊ ሚዲያ ወጥመዶች፦ በሽልማት፣ በስራ ማስታወቂያ ወይም በቴሌግራም/ዋትስአፕ በኩል የሚላኩ የማረጋገጫ ቁጥሮችን ለሌላ አካል መስጠት ለከፍተኛ ዝርፊያና ለወንጀል ተጋላጭ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ደንበኞች ስልካቸውን ለጥገናም ሆነ ለሌላ ጉዳይ ለሰው ሰጥተው ሲቀበሉ አጠራጣሪ መተግበሪያዎች (Apps) አለመጫናቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አሳስቧል። ይህ የጥንቃቄ መልዕክት የወጣው በዲጂታል የክፍያ አማራጮች ላይ የሚታዩ የማጭበርበር ድርጊቶችን ለመግታት ባንኩ እያደረገ ያለው ጥረት አካል መሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች እነዚህን መመሪያዎች በመተግበር ገንዘባቸውን ከማንኛውም የሳይበር ጥቃትና ዝርፊያ እንዲከላከሉ ጥሪውን አስተላልፏል።