20/09/2026
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የሠራተኞች ምልመላና ቅጥር ሂደቱ ፍጹም ግልጽ፣ ፍትሐዊና በውጤት ላይ ብቻ የተመሠረተ እንዲሆን ጥብቅ አሰራር ዘርግቶ እየሰራ ይገኛል።
በዚህ ሂደት ላይ በማንኛውም መልኩ ሕገ-ወጥ አሰራር፣ አድሎ ወይም የሙስና ሙከራ ተፈጽሟል የሚል ተጨባጭ መረጃና ማስረጃ ያላችሁ ወገኖች ጥቆማችሁን እንድታቀርቡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
መረጃችሁን ይዛችሁ መቅረባችሁ ለሥራችን እንደተደረገ ትልቅ እገዛና አጋርነት ይቆጠራል።
ከተማ አስተዳደሩ የሚቀርቡለትን ጥቆማዎች በጥልቀትና በገለልተኝነት መርምሮ ጥፋት በተገኘበት አካል ላይ የማያዳግም ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ሙሉ ዝግጁነቱን ያረጋግጣል።
ጥቆማና ማስረጃ ማቅረቢያ አድራሻዎች፦
• በነጻ የስልክ መስመር፦9977
• በቀጥታ የስልክ መስመሮች፦011 171 0281 / 011 171 0993 / 011 171 0477 / 011 171 0556
• በአካል፦ በከንቲባ ጽሕፈት ቤት የፀረ-ሙስና ግብረ-ኃይል
ከማህበራዊ ሚዲያ ይልቅ ችግሩን በተጨባጭና በሕጋዊ መንገድ መፍታት የሚችለው የከተማ አስተዳደሩ ነው!
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የሠራተኞች ቅጥር ሂደትን በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያ ለሚሰራጩ ሐሰተኛና መሠረተ-ቢስ መረጃዎች የተሰጠ ማብራሪያ
እንደሚታወቀው የከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ በአዲስ ላስገነባቸው ሆስፒታሎች ሠራተኞችን ለመቅጠር መመሪያው በሚፈቅደው መሠረት ግልጽ ማስታወቂያ አውጥቶ በቅጥር ሂደት ላይ ይገኛል። ሆኖም አንዳንድ ኃላፊነት የማይሰማቸው የማህበራዊ ሚዲያ አካላት የቅጥር ሂደቱን ለማደናቀፍ በሚመስል መልኩ ሐሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጩ ይገኛሉ።
በጉዳዩ ላይ እውነታውን ግልጽ ለማድረግ የሚከተሉትን ነጥቦች እናሳውቃለን፦
1ኛ. እስከ አሁን ድረስ ለተቋማቱ አዲስ ተቀጥሮ የተመደበ ምንም ዓይነት ሠራተኛ የሌለ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሎቹ ውስጥ እየሰሩ የሚገኙትም ከከተማ አስተዳደሩ ነባር ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች በውሰት የተመደቡ መሆናቸውን ማንኛውም አካል ማረጋገጥ ይችላል።
2ኛ. እየተሰራጨ ያለውን መሠረተ-ቢስ መረጃ ለማጀብ ሲባል በከተማ አስተዳደሩ በቀጥታ የማይተዳደሩና ቢሮው ቅጥር ፈጽሞላቸው የማያውቁ ተቋማት ስም ጭምር በዘገባው ተካቷል።
3ኛ. ቢሮው በጭራሽ የቅጥር ማስታወቂያ ያላወጣባቸው የሙያ ዘርፎች (ለምሳሌ፦ የድንገተኛ ቀዶ-ሕክምና ባለሙያ የመሳሰሉ በሆስፒታሎቹ የሙያ መደባቸው የሌለና በአሁኑ ሰዓት በውሰት እንኳ የማይገኙ ሙያዎች) እንደተቀጠሩ ተደርጎ ፍጹም ሐሰተኛ መረጃ ተሰራጭቷል።
በተጨማሪም ገና ለፈተና ያልተጠሩና ፈተና በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ እንደ ሰመመን ሰጪ (አንስቴዥያ) ባለሙያዎች ፈተና ወስደው እንደተቀጠሩ ተደርጎ ከመዘገቡ ባሻገር፣ የጨቅላ ሕጻናት ነርስ ባለሙያዎችን ጨምሮ በማንኛውም ሙያ ቅጥር ባልተፈጸመበት ሁኔታ ቅጥር እንደተከናወነ ተደርጎ መዘገቡ መረጃው ከእውነት የራቀ ፈጠራና ውንጀላ መሆኑን ያረጋግጣል።
ስለሆነም እየተሰራጨ ያለው መረጃ ተራ አሉባልታ መሆኑን እየገለጽን፣ ቢሮው አጠቃላይ የቅጥር ሂደቱን ግልጽነት በተሞላበት መልኩ ለመምራት የሚከተሉትን አሰራሮች ተግባራዊ አድርጓል፦
1. ለአገልግሎት አሰጣጡ ጥራትና ለሥራው ተገቢው እውቀት፣ ብቃትና ክህሎት ያላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ፣ ፈቃድ ሰጪ ተቋማት የሰጡትና የመጠቀሚያ ጊዜው ያላለፈ ወይም የታደሰ ሕጋዊ የሙያ ፈቃድ ያላቸው መሆን ግዴታ እንዲሆን ተደርጓል።
2. የምዝገባ ሂደቱ ከሰው ንክኪ ነጻ በሆነ መልኩ ሙሉ በሙሉ በበይነ-መረብ (ኦንላይን) እንዲከናወን ተደርጓል።
3. ከምዝገባ በኋላ መስፈርቱን አሟልተው ለፈተና የሚቀርቡ ተወዳዳሪዎች ስም ዝርዝር ማንኛውም ሰው ሊመለከተው በሚችልበት የቢሮው ይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ይፋ ይደረጋል።
ጥሪ በሚደረግበት ወቅትም መስፈርቱን አሟልተው ስማቸው ያልተካተተ ቢኖር እንኳ ቅሬታ የሚያቀርቡበት ሥርዓት ተዘርግቷል። በዚህም በተፈቀደው የምዝገባ ጊዜ ውስጥ በበይነ-መረብ ተመዝግበው የተጠየቀውን መስፈርት እስካሟሉ ድረስ ታይቶ ለፈተና የሚቀመጡበት ሁኔታ ተመቻችቷል፤ ከተቀመጠው አቅጣጫ ውጪ በምንም ዓይነት ሁኔታ ለፈተና የተቀመጠ ተፈታኝ የሌለ መሆኑን እናረጋግጣለን።
4. የፈተና ሂደቱ ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሆን በከተማ አስተዳደሩ ሥር በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለሙያዎች አማካኝነት እንዲሰጥ ተወስኖ፣ በየተቋማቱ የፈተና አሰጣጥ መመሪያው በሚፈቅደው መሠረት በጥንቃቄ እየተተገበረ ይገኛል።
በመሆኑም በቅጥር ሂደቱ ላይ እየተሳተፋችሁ ያላችሁ ክቡራን ተወዳዳሪዎች ፣ የምልመላና የቅጥር ሂደቱ በተወዳዳሪዎች የውጤት ብልጫ ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆኑን ተገንዝባችሁ በተረጋጋ መንፈስ እንድትወዳደሩ እናሳውቃለን።
በተመሳሳይ መልኩ ቢሮው በሚያከናውነው የሰው ኃይል ቅጥርም ሆነ ስምሪት ላይ ከሕግና ከመመሪያ ውጪ ስለመሰራቱ ትክክለኛ ማስረጃ ማቅረብም ሆነ ጥቆማ መስጠት የሚችል ማንኛውም አካል ለከተማ አስተዳደሩም ሆነ ለጤና ቢሮው በማንኛውም ሰዓት ማቅረብ እንደሚችል እንገልጻለን። እስከ አሁን ድረስ ከማንኛውም ሚዲያም ሆነ ግለሰብ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያለው ምንም ዓይነት ጥያቄም ሆነ ጥቆማ ያልቀረበልን ቢሆንም፣ ከየትኛውም ወገን የሚመጣን ጥቆማ ተቀብለን አስፈላጊውን ማጣራት ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን።