10/01/2026
የአራጣ ወንጀል በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ
መግቢያ
አራጣ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ የህሊናን ወይም የሰውን ችግር መሰረት በማድረግ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ስር የሚካትት ወንጀል ሲሆን አስቀጪነቱም በሕጉ ተደንግጓል። ይህ ድርጊት በማኅበረሰብ ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ በሕግም ሆነ በሞራል ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው። በዚህ ጽሑፍ የአራጣን ምንነት፣ በሕግ የተፈቀደን የወለድ መጠን፣ የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች እና የአራጣ ወንጀልን የሕግ ተጠያቂነት በአጭሩ እንዳስሳለን።
የአራጣ ምንነት
የሕግ መዝገበ ቃላት የሆነው ብላክስ ሎው መዝገበ ቃላት 8ኛው እትም እንደሚሰጠው ትርጉም ”USURY is an illegal contract for a loan or forbearance of money, goods, or things in action, by which illegal interest is reserved, or agreed to be reserved or taken.” ይህን ወደ አማርኛ በግርድፉ ስንመልሰው አራጣ ማለት ሕገ-ወጥ በሆነ የብድር ውል ወይም ገንዘብን፣ እቃዎችን ወይም በድርጊት ላይ ያሉ ነገሮችን መስጠት ሆኖ ሕጋዊ ያልሆነ ወለድ ለመጠበቅ ወይም ለመስጠት የሚደረግ ስምምነት ነው። በሌላ በኩል ማሪያም ዌብስተር የተሰኘው መዝገበ ቃላት አራጣን በተጋነነ የወለድ መጠን ገንዘብ ማበደር በማለት ይተረጉመዋል። በመሆኑም ከተለያዩ ትርጉሞች መረዳት እንደሚቻለው አራጣ ያልተገባ የወለድ ስሌት ተበዳሪዎችን በማስከፈል የሚፈፀም ድርጊት ነው፡፡ ተመጣጣኝ የወለድ መጠን ፋይናንስ ገበያው ወይም ብሔራዊ ባንኮች በሚወስኑት መሰረት ማሰብ ተገቢ ቢሆነም በሕግ ከተወሰነው የወለድ ምጣኔ በላይ ገንዘብ ማበደር በብዙ አገሮች ዘንድ ወንጀል ተደርጎ ተደንግጓል፡፡ ወንጀሉም አራጣ በመባል ይታወቃል፡፡
በሀገራችን በ1996 ዓ.ም በወጣው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ ለአራጣ ቀጥተኛ ትርጉም ባይሰጥም በአንቀጽ 712 በአራጣ ወንጀል የሚያስጠይቁ ተግባራትን ያስቀምጣል። ይኸውም ማንም ሰው የተበዳዩን ችግረኝነት፣ የበታችነቱን፣ ወይም የገንዘብ ችግሩን፣ ወይም መንፈሰ ደካማነቱን፣ ወይም ልምድ ወይም ችሎታ የሌለው መሆኑን መሰረት በማድረግ፡-
በሕግ ከተፈቀደው ወለድ በላይ ገንዘብ ያበደረው እንደሆነ ወይም
ካበደረው ገንዘብ ጋራ በግልፅ ተመጣጣኝነት የሌለው ንብረት በምትኩ እንዲሰጠው ያደረገው ወይም ቃል ያስገባው እንደሆነ የአራጣ ወንጀል በመፈፀም የሕግ ተጠያቂነት ይኖርበታል።
በመሆኑም በአጠቃላይ አራጣ ማለት በሕግ ከተፈቀደው በላይ የተጋነነ የወለድ መጠን በማስከፈል እና ከገንዘቡ ጋር ተመጣጣኝነት የሌለው መያዣ በመቀበል የሚደረግ የብድር ስምምነት ሲሆን ይህም የተበዳሪውን ሁኔታ ማለትም ችግረኝነቱን፣ የበታችነቱን፣ የገንዘብ ችግሩን፣ መንፈሰ ደካማነቱን... መሠረት በማድረግ የሚፈፀም ብዝበዛ" (Exploitation of distress) ነው፡፡
በሕግ የተፈቀደ የወለድ መጠን ስንት ነው?
በኢትዮጵያ በሕግ የተፈቀደውን የወለድ መጠን ስንመለከት የፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 1751 ሕጋዊ ወለድ (Legal Rate of Interest) ማለት በውል ያልተወሰነ ወለድ (ጥቅም) ከፋይ የሆነ ሰው በዓመት በመቶ ዘጠኝ (9%) ሂሳብ ይከፍላል ይላል። በተጨማሪም የፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 2479(1) የብድር ውል ተዋዋይ ወገኖች ተበዳሪው ሊከፍለው የሚገባው የወለድ መጠን በወር ወይም በቀን ሳይሆን በዓመት ከአስራ ሁለት በመቶ (12%) በላይ ሊበልጥ እንደማይችል ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ሕጉ የፈቀደው የብድር ውል ወለድ መጠን በዓመት 12% ድረስ ብቻ እንደሆነ እንገነዘባለን።
ይሁንና ይህ የወለድ መጠን በባንኮች እና በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ላይ ተፈፃሚነት የለውም። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ብድር አቅርቦት በተፈለገው መጠን መገኘትን፣ እንዲሁም የወለድ ተመንና ሌሎች ክፍያዎችን የመወሰንና የመቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው ሲሆን ብሔራዊ ባንክ በአዋጅ ቁጥር 591/2000 ዓ.ም አንቀፅ 5(4) እና በመመሪያ ቁጥር 12/2010 መሠረት የብድር ውል ለደንበኞቻቸው በሚሰጡበት ወቅት ላበደሩት ብድር የወለዱን ምጣኔ በራሳቸው እንዲወስኑ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የወለድ ተመን መመሪያ ቁጥር 295/2020 መሰረት በብድር እና በቅድመ ክፍያ ላይ የብድር መጠን በተመለከተ በእያንዳንዱ ባንክ በነፃነት የሚወሰን እንደሆነ ያስቀምጣል። በመሆኑም ባንኮች በሚሰጡት ብድር ላይ የሚታሰበው የወለድ ምጣኔ ከላይ በፍትሐብሔር ሕጉ እንደተመለከተው የወለድ ጣራው በዓመት እስከ 12% ብቻ ሳይሆን ከዛም በላይ ማድረግ ይችላሉ። በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከየካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ በተለያዩ የብድር ዓይነቶች ላይ ጭማሪ ያደረገ ሲሆን በተደረገው ማስተካከያ መሰረት፣ የግብርና ብድሮች እስከ 15.5%፣ የንግድ ብድሮች እስከ 18%፣ የወጪ ንግድ ብድሮች እስከ 14%፣ የግል ብድሮች ደግሞ እስከ 15% ጭማሪ ተደርጎባቸዋል። ስለዚህ አራጣ ማለት ሕጉ ከፈቀደው የብድር ወለድ መጠን በላይ ተዋውሎ ማበደር ማለት ነው፡፡
የአራጣ ወንጀል የሚያስከትላቸው ጉዳቶች
አራጣ በተበዳሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ተበዳሪዎች ለተበደሩት ገንዘብ እንዲከፍሉ የሚጠየቁት የወለድ መጠኑ በጣም የተጋነነ ስለሆነ ብድሩን መልሰው ሳይጨርሱ ጥሪታቸው ወይም በብድሩ ገንዘብ ሰርተው ያገኙትን ትርፍ አበዳሪው ስለሚወስድባቸው ለኪሳራ እና ለከፋ ድህነት ይዳረጋሉ፡፡ ተበዳሪዎች ጊዜያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ብለው በተበደሩት ገንዘብ ድህነትን ሸምተዉ ድሀ ሆነው ሲቀሩ፤ አበዳሪዎችም ምንም እሴት በኢኮኖሚ ውስጥ ሳይጨምሩ ሀብት የሚሰበስቡበት ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
የአራጣ ወንጀል በግለሰቦች ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ባለፈ የድርጊቱ መበራከት ሀገራዊ ጉዳት በማስከተል የሀገር ኢኮኖሚ ላይ ሊያደርስ የሚችለው ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይሆንም። በአራጣ የሚዘዋወረው ገንዘብ ላይ መንግሥት እውቅና ስለማይኖረው ከትርፉ ላይ ግብር ስለማይከፈል መንግሥት ገቢ ሳይሰበስብ ይቀራል፡፡
ሌላው ጉዳት ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ገንዘባቸውን ባንክ እንዳያስቀምጡ ከማድረጉ ጋር የተያያዘ ሲሆን ይህም የሚሆነው ጥቂትም ቢሆን ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ገንዘባቸውን ባንክ ከማስቀመጥ ይልቅ አራጣ በማበደር እንዲሰማሩ በማድረጉ ነው፡፡ ገንዘቡ በባንክ ተቀመምጦ ለኢኮኖሚው ሊያበረክተው የሚችለውን አስተዋጽኦ የሚያስቀረው ሲሆን ወደ ባንኮች የሚገባው ተቀማጭ እየቀነሰ መሄዱ በመጨራሻም ባንኮች አቅም እያጠራቸው እንዲሄዱ ያደርጋቸዋል፡፡ ባንኮች ለብድር የሚውል ተቀማጭ ገንዘብ ሲያጥራቸው በተዘዋዋሪ አራጣ አበዳሪዎች የብድር አማራጭ ይሆናሉ፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ በተመጣጣኝ ወለድ መጠን ገንዘብ ተበድረው ሥራ ሊሰሩ የሚችሉ ሰዎች ብድር ሳያገኙ እንዲቀሩ ያደርጋቸዋል።
የአራጣ ወንጀል የሕግ ተጠያቂነት
የአራጣ ወንጀል በወንጀል ሕጉ በአንቀፅ 712 ስር ሽፋን አግኝቷል። ከላይ እንደተገለፀው በድንጋጌው ላይ የዘረዘሩትን ተግባራት የፈፀመ ሰው በቀላል እስራት ወይም እንደነገሩ ሁኔታ ከ5 (አምስት አመት) በማይበልጥ ፅኑ እስራት እና በመቀጮ ይቀጣል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ማንኛውም ሰው ከላይ በተጠቀሰው ሀሳብ መነሻነት በአራጣ ላይ የተመሰረተ መብት የተቀበለ፣ በመከላከያነት የተጠቀመበት ወይም ለሌላ ሰው ያስተላለፈ እንደሆነ በተመሳሳይ ሁኔታ ይቀጣል፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ የአራጣ ወንጀል በማኅበረሰብ እና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ቀላል የሚባል ስላልሆነ ማኅበረሰቡ ብድርን በተመለከተ ሕጋዊ መንገድን መከተል እና ወንጀሉ ተፈፅሞ ሲገኘም ወንጀል ፈፃሚዎች እንዲቀጡ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል።
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ