29/05/2026
የበሬ ወለደ ሀሰት ዘመቻ የሥርዓቱን ነውር ቢገልጥ'ጂ ተጋግሮ ዳቦ አይወጣውም!
ከሰሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያ በሚናፈሰው ውሸት ዙሪያ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
ከሰሞኑ የእናት ፓርቲ ፕሬዝዳንትና የትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ም/ፕሬዝዳንት የኾኑት ሰይፈሥላሴ አያሌው(ዶ/ር) ከ አንከር ሚዲያ ጋር ቆይታ አድርገው ጠንከር ያሉ ሀሳቦችን በሰጡ ማግስት የብልጽግናው ተቀላቢ እንደ እብድ ውሻ ከፊቱ የቆመውን ኹሉ የሚናከሰው ስብስብ(በዳቦ ስሙ ሚዲያ ሠራዊት ወይም ዲጂታል ሸኔ) ከዋና ማዘዣው በጉሽ ወይን የጠጣውን መርዝ ዐይኑን እያጉረጠረጠ በሬ ወለደ ለሃጩን እያዝረበረበ ይገኛል።
ክቡር ፕሬዝዳንቱ ጠንከር ያሉ ሀሳቦችን በሰነዘሩ ማግስት ባልዋሉበትና እጅግ በሚፀየፉት ተግባር ሲብጠለጠሉ ከርመዋል። የብር ነገር ከተነሳ ዶ/ር ሰይፈ ሥላሴ በተገኙባቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ባልኾኑ ስብሰባዎች እንኳን ፈርመው አበል የተቀበሉበት አንድ አይገኝም ድንገት ለጠሪዎቹ ክብር ሲባል ከተገኘም ወደ ፓርቲው ካዝና በደረሰኝ አስገብተውታል። ኹሉም የፓርቲው አመራር እንደሚያውቀው ፓርቲው የገንዘብ ችግር ከገጠመው የመሙላት ሸክሙ በእርሳቸው ላይ የወደቀ ነው። በዚኽም ያልተመለሰላቸው በ100 ሺህ የሚገመት ገንዘብ ፓርቲው አለበት። እኛም እንስጥ አላልን እሳቸውም አምጡ አይሉም። ቢሮም ቢኾን ፓርቲያችን ብዙ ሺህ ብሮች ሊያስወጣ የነበረን ራሳቸው በሚያስተዳድሪሩት ሕንጻ በነጻ ከ 7 ወራት በላይ በነጻ ተጠቅሟል።
እርግጥ ክቡር ፕሬዝዳንቱ በየዓመቱ እንደሚያደርጉት ለእረፍትና ለግል የቴክኖሎጂ ጋር የተገናኘ ቢዝነሳቸውን ኹኔታዎችን ለማስተካከል ያንንም ለአመራሩ በውል አሳውቀውና ተፈቅዶላቸው ከወራት በፊት ወደ አሜሪካ ሄደዋል። ከሣምንት በፊትም ከብዙ ልፋትና ጥረት በኋላ በፓርቲው እውቅና፣ በአሜሪካ መንግሥት ሕጋዊ ሂደትን አሟልቶ የፓርቲው የሰሜን አሜሪካ ቻፕተር በተገኙበት አስጀምረዋል።
ስለኾነም ፓርቲው ያለበት እንጂ ክቡር ፕሬዝዳንቱ የወሰዱትም ንብረት ኾነ ገንዘብ የለም፤ ኖሮም አያውቅም።
የሥምሪቱ የምትሰጡ ጌቶች እብድ ውሾቻችኹን አባቶቻችን ሲያደርጉ እንደኖሩት ብዙ ሰው ሳይበክሉ ክትባት ብትሰጧቸው ወይም ቫይረሱ ተሠራጭቶ የማይድን ከኾነም ከማዘዣው ብታስገልሏቸው። በሬ ወለደ ሥርዓትን ይበልጥ ከማዋረድ የዘለለ ዳቦ አይኾን፣ አገር አያድን።
ፈጣሪ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!
እናት ፓርቲ- ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት
ግንቦት ፳፩ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ