26/10/2026
እንችላለን!
የከተማችን ብስራት የሆነው የተፈጥሮን ጸጋ ከዘመናዊ የከተማ ስልጣኔ ጋር አዋህዶ የነዋሪዎቿን የኑሮ ዘይቤ የሚያሻሽለውን የቀጨኔ–አምባሳደር–ጊዮን–ኢሬቻ ፓርክ እስከ ባምቢስ የሚዘልቀውን ግዙፍ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ለህዝባችን ክፍት ተደርጏል ።
በእርግጥም አዲስ አበባ የኢትዮጵያ የስልጣኔ አምባ እና የዘመናዊነትና የመደመር ምልክት ሆና ጐልታ የወጣችበት፣ መሰረተ ልማት ከአደራ ጠባቂነትና ከዜጎች ህይወት ጋር ተሰናስሎ የተገነባበት በከተማችን የመታደስ ታሪክ ውስጥ ትልቅ የታሪክ መታጠፊያ የሆነ ብሩህ ገጽ የተከፈተበት ጊዜ ነው::
ወንዞቻችን የከተማችን የትላንት ድብቅ ገመናዎቻችን መሸፈኛ ነበሩ፣ የከተማችንን ቆሻሻ ማጠራቀሚያ፣ ፍሳሽ እና መጸዳጃ ማስወገጃ፤ ለበርካታ ተላላፊ በሽታዎች እና ለህዝባችን ጤና መጓደል ጥልቅ መንስኤ ሆነው ኖረዋል።
ዛሬ ላይ ግን ያ ታሪክ ላይመለስ ተቀይሮ ወንዞቻችን ህይወት ዘርተዋል፣ የታመሙ ወንዞቻችንን ታክመው ከበሽታ ምንጭነት ወደ ጤና ማዕከልነት፣ ከቆሻሻ ማከማቻነት ወደ ውበት ሰገነትነት፣ ለመጠጋት ከሚፈራበት ወደ ማረፊያ ጊዜ ማሳለፍያና መዝናኛነት ተቀይረዋል።
አሁን ወንዞቻችን ዜጎች የደስታ ጊዜ የሚያሳልፉባቸው፣የጤና፣ የስፖርት፣ የንባብ፣ የኪነ-ጥበብ (የአርት)፣ የእረፍት እና የማህበራዊ መስተጋብር ማዕከላት፤ እንዲሁም ማህበረሰቡ የሚገበያይባቸው ማራኪ የከተማችን ጌጦች ሆነዋል።
ይህ ድንቅ ስፍራ ተፈጥሮን ከታሪክ፣ ዘመናዊነትን ከብዝሀነት ፣ውበትን ከጥራት ጋር አቀናጅቶ ለከተማችን ተጨማሪ ድምቀት ሆነዋል::