01/11/2024
ለአዲስ አበባ ማኅበራዊ ትረስት ፈንድ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ተሰጠ፡፡
ሥልጠናው በፕሮጀክት ዝግጅት፡ ማኔጅመንትና ትግበራ ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ ይህም ስለፕሮጀክት ምንነት፣ጠቀሜታና አዘገጃጀት እንዲሁም ጊዜን በአግባቡ አብቃቅቶ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የማነቃቂያ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡
አንድ ፕሮጀክት ሲቀረጽ ዓላማ ያለው ሲሆን፤በዋናነት አንዲን ችግር ለመቅረፍ በቂ ጊዜና በጀት ተበጅቶለት ጥራት ባለው መልኩ በመከናወን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሲጠናቀቅ ነው ሲሉ አሰልጣኙ አስገንዝበዋል፡፡
እንደዚሁም በሥነ-ምግባርና በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ላይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን፤ሥነ-ምግባር በሥነ-ምግባር ቅቡልነት የሌላቸውን ሠራተኞች የሚያስተካክል ልጓም ነው፡፡ ስለሆነም ሥነ-ምግባራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ልንሠራ እንደሚገባ ተገልጧል፡፡
ሥነ ምግባር ለሁሉ ነገር መሠረት በመሆኑ በቅንነትና ሙሉ ሰብዕና በመላበስ በታማኝነት፣ አክባሪነትና አድሎአዊነት በሌለው ሕዝብን ማገልገል እንደሚገባ ከሥልጠናው ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
አሁን እየታዬ ያለው የዕውቀት ችግር ብቻ ሳይሆን በቅንጅት የመሥራት ጉዳይ በመሆኑ በቅንጅት ከተሠራ ተቋማችንን ተወዳጅ፣ ተመራጭና ቀዳሚ ማድረግ ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰብአዊነትን በማስቀደም ኅሊናን ሊያረካ የሚችል አገልግሎት መስጠት ይገባል ተባሏል፡፡
የአዲስ አበባ ማኅበራዊ ትረስት ፈንድ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አሥራት ንጉሴ የተሰጡት ሥልጠናዎች ከተቋሙ ተልእኮና ራእይ አንጻር በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ በተለይ ሠራተኛው በነበረው ላይ ዕውቀቱን በሥልጠናው ስለሚያጎለብትና ስለሚያነቃቃ ይበልጥ ለአገልግሎት እንዲተጋ የሚያግዝ ነው በማለት በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ሥልጠናውን ለሰጡት አካላት ምስጋና አቅርበው ይህ ዓይነቱ ሥልጠና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡