23/01/2026
የንግድ ስራ ፈቃድ እድሳት ለተጨማሪ 15 ቀናት ተራዘመ።
የንግድ ስራ ፈቃድ እድሳት በበጀት ዓመቱ ከሀምሌ 1/2017 እስከ ታህሳስ 30/ 2018 ዓ/ም ድረስ ያለቅጣት የሚታደስበት ጊዜ እንደሆነ ይታወቃል።
አመታዊው የንግድ ፈቃድ እድሳት ያለቅጣት የሚታደስበት ጊዜ ካበቃበት ታህሳስ 30/2018 ዓም ጀምሮ የማደሻ ጊዜው ለተጨማሪ 15 ቀናት ተራዝሞ እድሳት ሲከናወን ቆይቷል።
ይሁን እንጂ በተሰጠው ጊዜ እድሳታቸውን ያላጠናቀቁ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የንግድ ስራ ፈቃዳቸውን እድሳት ማከናወን እንዲችሉ ለመጨረሻ ጊዜ ለተጨማሪ15 ቀናት መራዘሙን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አሳውቋል።
በተሰጠው ተጨማሪ ጊዜ መሰረት የንግድ ስራ ፈቃድ እድሳት ያለቅጣት የሚከናወንበት ጊዜ ጥር 30/2018 ዓም የሚያበቃ ይሆናል።
ለቀኑ መራዘም ምክንያት ነጋዴዎች የክሊራንስ አሰጣጥ ላይ መጓተቶች በመኖራቸው ክሊራንስ አለመጨረሳቸውን በመግለጽ ቅሬታ በማቅረባቸው ምክንያት መሆኑን ተገልጿል።
ቅሬታቸው በንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተቀባይነት በማግኘቱ ለተጨማሪ 15 ቀናት እስከ ጥር 30/2018 ዓም ድረስ ለመጨረሻ ጊዜ እንዲራዘም መወሰኑን ቢሮው አሳውቋል።
እንደ ንግድ ቢሮው መረጃ እስካሁን 295 ሺ 810 የሚሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት እድሳት አከናዉነዋል።
የንግድ ስራ ፈቃድ እድሳት አገልግሎት ከሠኞ-ቅዳሜ ከጠዋቱ 2፡30 እስከ ምሽቱ 2፡30 በኦንላይን እየተሠጠ የሚገኝ ሲሆን በቀሩት ቀናት ንግድ ፈቃዳቸውን ያላሳደሱ ነጋዴዎች እንዲያሳድሱ ቢሮው ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ