07/04/2022
✍የተራዊሕ ሶላት የረከዓ ብዛት
❔ጥያቄ፡
💫የተራዊሕ ንሶላት ግማሹ 20 ረከዓ ነው ፤ ግማሹ 8 ረከዓ ነው እያሉ በየዓመቱ ጭቅጭ ቅ እና ፀብ ይነሳል። 20 ረከዓ መስገድ ቢድዓ ነው, ሓራም ነውም ይላሉ፤ ይህ እንዴት ይታያል?
✅መልስ፡
⚡️በመጀመሪያ ደረጃ ንትርክ እና ጭቅጭቅ, ክርክር በዲኑ የተወገዙ ናቸው። ክርክር ያበዛ ሰው ዲኑ ላይ ፅናት አይኖረውም። ነቢዩ -ዐለይሂሶላቱ ወሰላም - [ሓቀኛ እንኳን ብሆን፤ ሐቁ እንኳን ያለው እሱጋር ቢሆን መከራከርን የተወ ሰው ጀነት እንደሚገባ እኔ ኃላፊ እሆነዋለው ]ብለዋል ነቢዩ -ዐለይሂሶላቱ ወሰላም። ሓቅን ተናግሮ ማለፍ እንጂ መከራከር አያስፈልግም, መጨቃጨቅ አያስፈልግም። እንደዚሁ ደግሞ "ኺላፍ" ያለበት, የሓሳብ ልዩነት ሊከሰት የሚችልበት ነጥብ ላይ እዚህ ደረጃ የደረሰ ፀብን ሊያስከትል የሚችል "ኺላፍ" ውስጥ መግባት አያስፈልግም። "ኺላፍ" መብዛቱ የቀልብን መራራቅ ያስከትላል። የፊቅህ ጉዳይ ላይ "መኻለፍ"/(መለያየት) ከሶሓቦች ዘመን ጀምሮ ያለ ነው። "ኢነማ" የሚወገዘው በሶሓቦች ዘመን ያልነበረው የዐቂዳ "ኺላፍ" ነው ያልነበረው። ዉዱእ የሚያፈርሱ ነገሮችን በተመለከተ፣ አንዳንድ መብላት የሚቻል እና የማይቻል ነገሮችን በተመለከተ፣ ፊቅህ ነክ ነጥቦች ላይ ከጥንት ጀምሮ "ኺላፍ" አለ። ልባችን ሰፊ ሊሆን፣ የሌላኛውን ወገን ማስረጃ ልናደምጥ ፣ልንረጋጋ ዓላማችን ለሰዎች ሓቅን ማሳወቅ ሊሆን ይገባናል። የተራዊሕ ሶላትን ቁጥር በተመለከተ ሰዎች ለሁለት ተከፍለዋል, በተለይ አላዋቂዎች። የተወሰኑት ከ11 ረከዓ በላይ መጨመር ስሕተት ነው ,ወንጀል ነው , ቢድዓ ነው ያሉበት ሁኔታ አለ። ሌሎች ደግሞ 11 ብቻ መስገድን ያወገዙበት አጋጣሚ አለ፤ ሁለቱም ስሕተትነው። ጥያቄው ላይከ 11 በላይ መጨመር ቢድዓ ነው, ሓራምም ነው ሁሉ እያሉ ነው የሚል ቃል አለ፤ እንዴት ተብሎ ነው 11 ላይመጨመር ሓራም የሚሆነው? ቢድዓ የሚሆነው? ነቢዩ-ዐለይሂሶላቱ ወሰላም -ስለ "ሶላተ-ለይል"/(የሌሊትሶላት) ሲጠየቁ [የሌሊት ሶላት ሁለት ሁለት ረከዓ ነው፤ ይነጋብኛል ብሎ የፈራና የሰጋ ሰው አንድ ረከዓ ይጨምር ዊትር ይሆንለታል።] ብለው ሳለ። ጠያቂው የለይል ሶላትን አሰጋገድ ብዛቱንም ጭምር ነው የጠየቃቸው። ነቢዩ (-صلى الله عليه وسلم) ይህን ያክል ሰግደህ አቁም አላሉትም፤ የሌሊት ሶላት ሁለትሁለትረከዓነው ያሉት፤ጥጉን አልነገሩትም። በዚህ መሰረት ከፈለጉ 20ረከዓ, ከፈለጉ 40ረከዓ, ከፈለጉ 80 እና 100 ረከዓም ቢሆን መስገድ እንደሚቻል ነው ሓዲሱ የሚያሳየው፤ የሌሊት ሶላት ገደብ የለውም። በመሆኑም ነገሩን ልናጠበው, ልናጠብቅ አይገባም። ከደጋግ ቀደምቶች ውስጥ እጅግ በጣም በርካታ የዲን መሪዎች ከ11 በላይ መጨመር እንደሚቻል ተናግረዋል። ከ11በላይ ሰግደዋል; አሰግደዋል። ከ11 በላይ መስገድ አይቻልም እያሉ10 ከተሰገደ በኃላ ጥለው የሚወጡ ወይም እዛው ቁጭ ብለው ሶፍፉ ክፍት እንዲሆን የሚያደርጉ ወይም ወደ ኋላ ሄደው ወሬ እያወሩ ሰውን የሚረብሹ ሰዎች ትልቅ ስሕተት ላይ ወድቀዋል። እንደዚሁም ደግሞ ትልቅ አጅርም አልፏቸዋል። ኢማሙ ሶላቱን እስኪጨርስ አብሮ የሰገደ ሌሊቱን በሙሉ ሲሰግድ እንዳደረ ይቆጠርለታል በሚለው በነቢዩ (-صلى الله عليه وسلم -) ሓዲስ የተነገረው ትሩፋት ይቀርባችዋል። እንደዝሁ ደግሞ ከ11 በላይ መጨመርም አይቻልም ብለው በማመናቸው ፤ይህ ቢድዓ ነው በማለታቸው ስሕተተኛም ይሆናሉ። ይህ እንዳለ ሆኖ 11 ብቻ የሚሰግዱ ሰዎችንም የሚያወግዙ አሉ፤ ይሄም ስሕተት ነው። ነቢዩ-ዐለይሂሶላቱ ወሰላም - ዓኢሻ (-ረዲየሏሁዐንሃ-) እነደተናገሩት፦ "ረመዷንም ይሁን ከረመዷንውጪ 11 ረከዓ ነበር የሚሰግዱት"። 11 መስገድ ይቻላል፤ ሱንናም ነው። ከ11 መጨመርም ይቻላል፤ ሁለቱም ትክክል ነው። እንዴት ነቢዩ-ዐለይሂሶላቱ ወሰላም -ከ11 በላይ ሰግደው የማያውቁ ከመሆኑም ጋር ሁለቱም ይቻላል ይባላል? (ከተባለ) ነቢዩ-ዐለይሂሶላቱ ወሰላም -ቂያሙን፣ ሩኩዑን፣ ሱጁዱን እያረዘሙ ነበር የሚሰግዱት። እንደነብዩ (-صلى الله عليه وسلم -) አርዝሞ መስገድ የቻለ ሰው "መእሙሞቹ"/(ከኋላ የሚሰግዱት ተከታዮቹ) ፍቃደኛ ከሆኑ11 መስገዱ በላጭ ነው ይባላል። ነገርግን ይሄን ማድረግ ለመእሙሞች የሚከብዳቸው ከሆነ አጠር አድርገው እየቀሩ ብዙ ረከዓ ቢሰግዱ ምንም ችግር የለውም። ነብዩ (-صلى الله عليه وسلم -) በተግባራቸው 11 ቢሰግዱም በንግግራቸው የሌሊት ሶላት ሁለት ሁለት ረከዓ ነው ብለዋል አልገደቡትም። 11 መስገዳችው ከ11 በላይ መስገድ እንደማይቻል የሚያሳይ "ደሊል"/(ማስረጃ) አይደለም። የነብዩ(-صلى الله عليه وسلم -) ንግግር እና ተግባራቸው ከተጋጨ የሚቀደመው ንግግራቸው ነው። የሌሊት ሶላት ሁለት ሁለት ረከዓ ነው ብለዋል፤ እዚህ ጋር ደግሞ ተጋጨ የሚያስብል ደረጃም የደረሰ አይደለም። ሓዲሱን ደጋግ ቀደምቶች, ዑለሞች በተረዱት መልኩ ነው ልንረዳት የሚገባው። 11 ብቻ መስገዳቸው ከዚያ በላይ መስገድ እንደማይቻል የሚያሳይ ነው ብለው አልተረዱትም ደጋግ ቀደምቶች። ከሓነፍዮች፣ ከሻፍዕዮች፣ ከማሊኪዮች፣ ከሓንበልዮች ከአራቱም የዲን መሪዎች ታላላቅ የዲን ሊቃውንት ከ11 በላይ መስገድ እንደሚቻል ገልፀዋል። ሓነፍዮች ስለ ተራዊሕ ሲናገሩ |'فإنهاعشرون ركعة سواى الوتر عندنا'|ብለዋል|" ተራዊሕ እኛ ዘንድ ከዊትሩ ውጪ 20 ረከዓ ነው የሚሰገደው "ብለዋል። ኢማሙ -ነወዊም በሻፍዕያ መዘሃብ ዘንድ ተራዊሕ 20 ረከዓ እንደሆነ ተናግረዋል። ከሓንበልዮችም እብኑ ቁዳማም እንደዚሁ ኢማሙ አሕመድ የመረጡት ሶላቱ-ተራዊሕ 21ረከዓ እንደሚሰገድ ነው ብለዋል። ኢማሙ ማሊክ ረሒመሁሙሏሁ ተዓላ 36 መስገድ እንደሚቻል ተናግረዋል፤ማሊኪዮችም ይሄንያደረጉነበር። ስለዚህ ሶላተ-ተራዊሕ በመሰረቱ ሱንና ነው። ቁጥሩን በተመለከተ ገደብ የለውም። አራቱም መዘሃቦች ከ11 ረከዓ በላይ መስገድ እንደሚቻል ተናግረዋል። ደጋግ ቀደምቶች ከ11 በላይ ሰግደዋል፤ የረሱልን (-صلى الله عليه وسلم -) ሓዲስ ሓሳባቸውን ከኛ በላይ እነሱ ናቸው የሚያውቁት። በመሆኑም ከ11 በላይ መስገድ ቢደዓ ነው ፤ ከ20 መቀነስ ቢደዓ ነው ,ስህተት ነው ልንል አይገባም። ሁሉም ያስኬዳል፤ ዋናው ነገር በሱንናው መሰረት ሌላ ነገር ሳይጨምሩ መስገድ ነው።
አላህ ይበልጥ ኣዋቂ ነው!!!
በሸይኽ አህመድ ሸይኽ አደም(حفظه الله)
https://t.me/ALIYMESJIDYOUTH