26/05/2026
“ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም!!” በኢትዮጵያ
ባለፉት የለውጥ አመታት መንግስት እጅግ ስር የሰደዱና ውስብስብ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት፣ ለበርካታ ዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲንከባለሉ የመጡ፣ ሃገር የምትጠገን የማትመስልባቸው በርካታ ስብራቶችን ለመጠገን የሚያስችሉ ከእሳቤ ጀምሮ በተግባር የተደገፉ ስራዎችን መንግስት በቁርጠኝነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ሃገርን ከተረጂነትና ከልመና የሚያላቅቁ፣ ትውልዱ ቀና ብሎ እንዲሄድ የሚያግዙ፣ ፈጣንና ውጤታማ ስራዎች ተጀምረዋል፡፡ አስደናቂ ውጤትም እያስገኙ ነው። ከእነዚህ ተግባራት አንዱ ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም ኢኒሼቲቭ ነው::
እሳቤው በምግብ ሉዓላዊነት ማዕቀፍ ውስጥ የሰብአዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን በሁለት ዓመታት (2017-2018) ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ የመንግስት ደፋር ውሳኔ የታሪክ እጥፋትና ጨዋታ ቀያሪ ሲሆን ለአህጉራችን የብልጽግና ተምሳሌት ያደርገናል፡፡
ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ማዕቀፍ የሚፈጸም ቢሆንም ብሔራዊ ደህንነትን፣ ማህበራዊ ፍትሕን፣ ሰብአዊ መብትን አዎንታዊ ሰላምንና ዘላቂ ልማትን የምናሳካበት እሳቤ ነው፡፡ በተፈጥሮአዊና ሰው-ሰራሽ ምክንያቶች ጊዜያዊ ሰብአዊ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎችን በሀገር-በቀል አቅም መታደግ ማለት ነው፡፡ ይህም ዜጎቻችን በተቸገሩበት ቅጽበታዊና ነባራዊ ሁኔታ በመንግስት አቅምና በማኀበረሰቡ አጋርነት ለኑሮ የማይመቹ አጋጣሚዎችን መሻገር መቻልን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም (የሰብአዊ ድጋፍ ሉዓላዊነት) እሳቤው ከውጭ አካላት የተንጠራራ፣ ጠባቂነትና ጥገኝነት መላቀቅን በዋናነት ቢያመላክትም ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ፣ ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልል በቅድመ-ተከተል አንዱ በሌላኛው የአስተዳደር እርከን ከጠባቂነትና ከጥገኝነት መላቀቅንም የሚያካትት ነው፡፡ በዚሁም የተሟላ ክብራችንን፣ ነፃነታችንንና ሉዓላዊነታችንን በአስተማማኝ ለማረጋገጥ የሚደረግ መደላደል እንደሚፈጥርና የሰላማችንና የልማታችን አካል መሆኑን በመረዳት ነው፡፡
መንግስት ይህንን ሁኔታ በቅድሚያ በመረዳት ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም የሚያሳልጡ የፖሊሲና የትግበራ ሕጎችን በመደንገግና ሀገራዊ የትግበራ ፍኖተ ካርታ በመንደፍ ከማንኛቸውም ጊዜ በላይ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡የሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅምን ለማረጋገጥ የሚሰሩ አምስት ፓኬጆችን ወይንም ዋና ዋና ተግባራት
1. የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ
“ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም” (Humanitarian Relief Sovereignty) አጀንዳ ሲነሳ የታሪክ እጥፋትና ጨዋታ ቀያሪ የሚባለው አስተማማኝ፣ ተደራሽና ተገማች የፈንድ ስርዓት ስለሚረጋገጥ ነው፡፡
መሠረታዊ እሳቤው በሀገር-በቀል አቅም ሰብአዊ ድጋፍን ማሟላት የሚቻለው አስተማማኝ የፈንድ አቅም ሲኖር ብቻ ነው የሚል ነው፡፡
የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ከዚህ በፊት የመንግስት ሚና ብቻ ሆኖ የቆየውን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር የሁሉም ዜጋና ተቋማት ኃላፊነት በማድረግ አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ መፍጠር ነው፡፡ የግልና የማኀበራዊ ተቋማት በስፋት የሚሳተፉበት ነው።
2. የመጠባበቂያ ምግብ ክምችት
የሰብአዊ ድጋፍ መጠባበቂያ ክምችት እንደ አገር ሊያጋጥመን የሚችለውን የግለሰብ፣ የቤተሰብና የማኀበረሰብ የተራዘመ የእህል እጥረትን ለመቋቋምና ለመሻገር የሚያስችል አቅም ነው፡፡ ይህ የክምችት አቅም በአገር ደረጃ 500,000 ሜትሪክ ቶን እንዲያዝ በመነሻ የተያዘ ሲሆን እያንዳንዱ ክልልና የተዋረድ መዋቅር ድርሻውን ተጋላጭ ቢሆንም ባይሆንም ማከማቸት ይጠበቅበታል፡፡
3. የሰብአዊ ድጋፍ ማከማቻ መጋዘኖች
ሁለተኛው ጉዳይ የሰብአዊ ድጋፍ ምግብ እና ምግብ-ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ማከማቻ መጋዘኖች ናቸው፡፡ ለመጠባበቂያና ለዕለት ደራሽ የሚያዙ ክምችቶች በተሟላ ጥራትና ሁኔታ ሊጠበቁ ይገባል፡፡ የብክለትና ብክነት ሁኔታዎች እንዳያጋጥሙ ከፍተኛ ጥንቃቄና እንክብካቤ ይሻል፡፡ የሙቀትና የቅዝቃዜ ሁኔታ፣ የወለል፣ የጣሪያና የግድግዳው አሠራር ለክምችት አደራደር በሚሆን መንገድ በባለሙያ ምክረ-ሀሳብ መሠረት የሚገነባ ይሆናል።
4. የቅጽበታዊ አደጋዎች አገልግሎት
ወጥ የሆነና በማኑዋል የሚመራ የኦፕሬሽን አቅም፣ የሎጅስቲክስ ክምችትና የአስቸኳይ ጊዜ የማስተባበርና የማቀናጀት ስርዓት ተዘርግቶ ተግባራዊ ማድረግ ይፈልጋል፡፡ በቅጽበታዊ አደጋዎች ወቅት ሁሉም ዜጋና ማንኛውም ተቋም በሚመለከተው አካል በሚሰጠው ምክረ-ሐሳብ መሠረት መተባበርና ድርሻውን መወጣት በህግ መሠረት ይገደዳል፡፡
5. የቤተሰብ ኃላፊነትና የማኀበረሰብ አጋርነት
“ሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም” የሕዝባችን መልካም ልምምድ መነሻ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህን መልካምና በጐ ልምምድ ለአደጋ ስጋት ስራ አመራር ተልእኮ ለማዋል የሚጠይቀው በማህበረሰብ ደረጃ የአመራር ስርዓቱን ግንዛቤ ማጎልበት፣ የአደረጃጀት ሚና ማስተዋወቅና አሠራሮችን ማበጀት ነው፡፡