29/05/2026
ሀገር ተረካቢ፣ብቁና ጤናማ ዜጋ ለማፍራት የበለፀገ የአመጋገብ ሥርዓትን መተግበር ይገባል፦አቶ አድማሱ አወቀ
በክልሉ Human capital operation( HCO) ፕሮጀክት ለሚደገፉ ዞኖችና ወረዳዎች ላሉ ባለሙያዎች የምግብና ሥርዓተ- ምግብ ትግበራን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱ ተመላክቷል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ግብርና ቢሮ እርሻ ልማት ዘርፍ በክልሉ Human capital operation( HCO) 0ፕሮጀክት በሚደገፉ ዞኖችና ወረዳዎች ላሉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት የሥርዓተ-ምግብ ተኮር ፣የምግብ ደህንነት ጥራትና የድኅረ -ምርት ቴክኖሎጂ አተገባበር ስልጠና መሰጠቱ ተገልጿል።
ሀገር ተረካቢ ፣ ብቁና ጤናማ ዜጋ ለማፍራት የበለፀገ የአመጋገብ ሥርዓትን መተግበር እንደሚገባ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእርሻ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ በስልጠና መድረኩ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር አመላክተዋል።
ኃላፊው በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን መጨመር በቤተሰብ ደረጃ በሚተገበረው ሥርዓተ-ምግብ ሂደት ላይ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን ገልፀው የተመጣጠነ የአመጋገብ ሥርዓት ያለው ማህበረሰብ ከመፍጠርና ጤናውን ከመጠበቅ ባለፈ በተሰማራበት የስራ መስክ ሁሉ ውጤታማ እንዲሆን ይረዳል ብለዋል።
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት እንደ ሀገር 40 በመቶ የሚሆኑ ህፃናት የመቀንጨርና የመቀጨጭ አደጋ ይታይባቸዋል ያሉት አቶ አድማሱ ይህንንም ለመቀነስ በቤተሰብ ደረጃ የአመጋገብ ሥርዓታችንን በማስተካከል በትምህርቱ ፣በፓለቲካው ፣ በኢኮኖሚውና በማኅበራዊ ጉዳይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመቀነስ በጋራ መሥራት ይገባል በማለት አሳስበዋል።
ከምግብና ሥርዓተ-ምግብ ችግሮች ጋር ተያይዘው የሚመጡ ጉዳቶችን ለመቀነስ የግብርናው ዘርፍ የተጣለበትን የማምረት ግብ ማሳካት ተገቢ ነው አቶ አድማሱ የተመረተው ምርት ጥራቱና ደህንነቱ ተጠብቆ ተመጋቢው ጋር እስኪደርስ ድረስ የብዙ የባለድርሻ አካላት ትብብርን ይጠይቃል ብለዋል፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ከፍተኛ ባለሙያ ወ/ሮ ነፃነት ካሳ በበኩላቸው ዠhuman capital operation project (HCO) ዋነኛ ዓላማ በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚታዩ የመቀንጨርና የመቀጨጭ ችግሮችን በመከላከል የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል ማሻሻል ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ለዚህም በግብርናው ዘርፍ የምግብ አቅርቦትን መጨመር ለሥርዓተ-ምግብ ትግበራ ያለው ሚና የጎላ በመሆኑ ደህንነቱ የተጠበቀ እና የተሰባጠረ በአንድ ገበታ ቢያንስ 4 እንዲሁም በቀን 6 የተሻለ ይዘት ወይም ጠቀሜታ ያላቸውን ምግቦች በመጠቀም የአመጋገብ ሥርዓታችንን መጠበቅ ይገባል ብለዋል።
በቀጣይም ከስልጠናው የተገኘውን ግንዛቤ በመጠቀምና በፕሮጀክቱ በሚደገፉ አካባቢዎች የተመደበውን በጀት ለታለመለት ዓላማ ብቻ በማዋል የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ ሊሠራ ይገባል በማለት ወ/ሮ ነፃነት ተናግረዋል።
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ሳይንስና ስነ -ምግብ ተመራማሪ ዶ/ር አምስቱ ኩማ በምግብ ደህንነትና ጥራት ርዕስ የተዘጋጀ የስልጠና ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን የክልሉ ግብርና ቢሮ ከፍተኛ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ጤናው ይሁነው የድኅረ- ምርት አሰባሰብ ቴክኖሎጂን አስመልክቶ የተዘጋጀ ሰነድ አቅርበዋል።
ጎፋ፣አሪና ኮንሶ ዞኖች ሰሜን አሪ ፣ መሎ ኮዛና ሰገን ዙሪያ ወረዳዎች በክልሉ ካሉ ዞኖች የመቀጨጭና የመቀንጨር ችግር ይበልጥ የታየባቸው አካባቢዎች መሆናቸው በጥናት ተለይተው በhuman capital operation (HCO) እየተደገፉ እንደሆነም ተገልጿል።
በቀረቡ ሰነዶችና በተሠጠው ስልጠና ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ከቤቱ በርካታ ጥያቄዎችና ሀሳቦች ተነስተው ከቤቱ ምላሽና ማብራርያ ተሰጥቶበታል።
የስልጠናው ተሳታፊ ከሆኑት አንዳንዶቹ እንደገለፁት የተሰጠው ስልጠና በቀጣይ ለሚሠሩት ሥራ የተሻለ ግንዛቤ ያገኙበትና ከቤተሰባቸው ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል አቅም እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
በመድረኩም የክልሉ ግብርና ቢሮ የእርሻ ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ፕሮጀክቱ የሚሠራባቸው ዞኖች የግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊዎች እና የወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ባለሙያዎች፣የዞንና የወረዳ የትምህርት ፣የጤና ፣የውኃና የሴቶች ተወካይና የፕሮጀክቱ ፎካሎች መሳተፋቸው ተዘግቧል።
በዝናቧ ጌታሁን