03/06/2026
በየደረጃው ያለው አመራር ህዝቡን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመታከት ሊሰራ ይገባል፦ ክቡር እንደሻው ጣሰው (ዶ/ር)
ወራቤ፣ ግንቦት 26/2018 (ስልጤ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን)
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር እንደሻው ጣሰው (ዶ/ር) በወራቤ ከተማ ከሰንበት እስከ ሰንበት ዘመናዊ የገበያ ማዕከልና መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
መርሃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ ሀገራችን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊና ውጤታማ በሆነ መንገድ ማከናወኗን በማንሳት ምርጫውን በማሳካት ሂደት የድርሻቸውን ለተወጡ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ከምርጫው በፊት በርካታ ውጤታማ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ይኼው ተግባር ተጠናክሮ ሌሎች ፕሮጀክቶችን የማስመረቅ መርሃ ግብር መቀጠሉን ተናግረዋል።
በምርጫ ማግስት ፕሮጀክቶችን ማስመረቅና ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል አዲስ ባህልና ልምምድ መሆኑን በማንሳት ይህ ልምድ የህዝብን ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ ከተወሰደ ቁርጠኝነትና ከተሰሩ ተከታታይ ስራዎች የተገኘ ውጤት መሆኑን አመላክተዋል።
በወራቤ ከተማ የተመረቀው ዘመናዊ የገበያ ማዕከል የአቅርቦትን እጥረትን በመፍታት የህብረተሰቡን የገበያ አማራጭ ለማስፋትቫ እንደሚያግዝ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
በሌላም በኩል በከተማዋ የተመረቀው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የተጀመረው ሀገራዊ ኢንሼቲቭ አካል መሆኑንና በቀጣይ ቀናት የሆሳዕናና ወልቂጤ ማዕከላትን ጨምሮ በሌሎች የክልሉ ከተሞች አገልግሎቱን የማስጀመር ስራ እንደሚሰራ አስረድተዋል።
በሁሉም ዘርፎች የተጀመሩ የተቀናጁ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹት ዶ/ር እንደሻው በየደረጃው ያለው አመራር ለህዝብ ተጠቃሚነት ያለመታከት እንዲሰራ አሳስበዋል።
የስልጤ ዞንና የወራቤ ከተማ አስተዳደር አመራር አካላት ለተሻለ ለውጥ ያላቸውን ቁርጠኝነት በማድነቅ የተጀመሩ ሰፋፊ ስራዎች ይበልጥ ጎልብተው እንዲቀጥሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ጠይቀዋል።