06/08/2025
የታክስ ማጭበርበር ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ የ8 ዓመት ከ4 ወር ጽኑ እስራት እና የ40,000 ብር ቅጣት ተፈረደበት።
አርባ ምንጭ፣ ሐምሌ 30/2017 ዓ.ም
የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጆችን በመጣስ የተከሰሰውን አቶ አብደላ እንድሪስን የ8 ዓመት ከ4 ወር ጽኑ እስራት እና የ40,000 ብር የገንዘብ መቀጮ ወሰነ።
በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የቆላ ሸሌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ አብደላ እንድሪስ በወረዳው በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ዘርፍ ተሰማርቶ የነበረ ሲሆን፣ የጋሞ ዞን ታክስ አስተዳደርና ገቢዎች ዐቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ መሰረት፣ የተጭበረበሩ የታክስ ሰነዶችን ለገቢ ተቋም በማቅረብ እና ታክስ በመሰወር ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።
በመዝገብ ቁጥር 50216 የተመዘገበው ይህ ክስ፣ ተከሳሹ የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 118/1(ሐ) እና 125/1ን መተላለፉን ያመለክታል።
ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት በሰውና በሰነድ ማስረጃዎች የጥፋተኝነት ድርጊቱ መረጋገጡን ተከትሎ በተከሳሽ አቶ አብደላ እንድሪስ ላይ የ8 ዓመት ከ4 ወር ጽኑ እስራት እና የ40,000 ብር የገንዘብ መቀጮ ወስኖበታል።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ታክስ መሰወር በህግ የሚያስቀጣ ከባድ ወንጀል መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን፣ ሌሎች ግለሰቦችም ከመሰል ህገ-ወጥ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ መልዕክት ያስተላልፋል።
(አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት)፦