23/04/2024
የሐዋሳ ከተማ ገቢዎች ባለስልጣን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በገቢ አሰባሰብ ላይ የተሰሩ ስራዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
የሐ/ከ/አስ/የመ/ኮ/ጉ/መምሪያ
ሚያዚያ 14/2016 ዓ/ም
ሐዋሳ
ሐዋሳ ከተማ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መልኩ ማርቆስ እንደገለጹት ሐዋሳ ከተማ በራሷ የገቢ ምንጭ ሙሉ ወጪዋን የምትሸፍን ከተማ መሆኗን የገልጸው በከተማ ደረጃ የልማት ጥያቄዎችን በጥራትና በፍጥነት መመለስ የሚቻለው ገቢን አሟጦ መሰብሰብና በተገቢው ጥቅም ላይ ማዋል ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም ለህብረተሰቡ የኘሮጀክት ስራዎች፣ ስራ ማስኬጃ፣ ደመወዝ ወዘተ የሚከናወኑት ከከተማዋ ከሚገኝ ገቢ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው በአሰባሰብ ሂደቱ እስከሁን የመጣንበትን መንገድ ልንቀይር ይገባል ብለዋል።
በ2016 በጀት ዓመት ከመደበኛውና ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ለመሰብሰብ ከታቀደው 4.2 ቢሊዮን ብር ውስጥ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2.4 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን የገለፁት አቶ መልኩ በዚህም ከ9ኝ ወሩ እቅድ 80% እንዲሁም ያልተሰበሰበ 20% እንደሆነ ገልጸዋል።
ገቢን አሟጣ ያለመሰብሰብ ችግሮች እንዳለ የገለጹት ኃላፊው ለዚህም እንደምክንያት ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ደረሰኝ አለመስጠት፣ በተገቢው የግል ተቋማት የሠራተኞችን ግብር፣ የጣራና ግድግዳ፣ የተከራይና የአከራይ ግብር የታክስ ግዴታን አለመወጣት እና በሌሎችም መሆኑን አክለዋል።
አቶ መልኩ አያይዘውም እንደ ከተማ ለሚሰበሰበው ገቢ ደሰረኝ መስጠት ግዴታ ያለባቸው የደረጃ"ለ" እና "ሀ" ግብር ከፋዬች በሚያከናውኑት ወቅት የግብይት ደረሰኝን በተገቢው አለመስጠት በገቢ አሰባሰቡ ረገድ ተግዳሮት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ ለህግ ተገዢ በመሆን ለሚፈፅመው ሽያጭ እና አገልግሎት ደረሰኝ በመቁረጥ ሸማቹም ለሚፈፅመው ግዥና አገልግሎት ደረሰኝ በመጠየቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ያሉት ኃላፊው ተቋሙ ግንዛቤ የማስጨበጥና የድጋፍና ክትትል ስራዎችን በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል::
አቶ መልኩ አክለውም ከዚህ በኋላ በየትኛውም ሁኔታ በከተማዋ ደረሰኝ የማይሰጥ፣ የማይቀበል እና ግብርን በወቅቱ የማይከፍል ማህበረሰብ ሊኖር አይገባምም ነው ያሉት።