02/07/2023
የንግድ ሥራ ፈቃድ አጠቃምን አስመልክቶ ሕጉ ምን ይላል?
@ትርጓሜ፤
የንግድ ሥራ ፈቃድ አንድን በሕግ የተፈቀደ የንግድ ተግባር/ሥራ ለማከናወን የሚያስችልና አግባብነት ካለው ፈቃድ ሰጪ አካል የሚሰጥ ፈቃድ ነው፡፡ በመደበኛነት የንግድ ፈቃድን የሚሰጡ አካላት ሁለት ሲሆኑ እነዚህም በፌደራል መንግስት ደረጃ የንግድ ሚኒስቴር ሲሆን በክልል ደረጃ ደግሞ የንግድ ቢሮ ናቸው፡፡
ከነዚህ ሁለት አካላት በተጨማሪ የንግድ ፈቃድን የሚሰጡ ሌሎች አግባብነት ያላቸው የአስተዳደር አካላትም አሉ፡፡ እነዚህ አካላት ከሥራው ልዩ ባህሪ አንጻር ፈቃዱን ለመስጠት የሚያስችሉ ልዩ የብቃት ማረጋገጫዎችን የሚጠይቁ ከመሆናቸውም ባሻገር የንግድ ሥራውን ለመምራትና ለመቆጣጠር ራሱን የቻለ ሙያዊ ችሎታን ስለሚጠይቁ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የማዕድን ፍለጋና ልማት ሥራዎችን በመለከተ ፈቃድ የሚሰጠው የማዕድን ሚኒስቴር/አግባብነት ያለው የክልል አካል ነው፤ የሚዲያ ሥራዎችን በተመለከተ የንግድ ሥራ ፈቃዱን የብሮድካስ ባለስልጣን ይሰጣል፤ የባንክ፣ የመድን እና የማይክሮ ፋይናንስ ንግድ ሥራዎችን ደግሞ ብሄራዊ ባንክ ፈቃድ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ሌሎች አካላትም አሉ፡፡
- ይዘት፡-
የንግድ ሥራ ፈቃድ የተለያዩ መረጃዎችን የያዘ ሠነድ ነው፡፡ የንግድ ሥራ ፈቃድ በይዘት ደረጃ የነጋዴውን/የድርጅቱን ስም፣ የሚሰራውን ሥራ፣ አድራሻውን፣ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር (TIN)፣ የሰጨውን አካል ማንነት፣ የተሰጠበትን ጊዜና የመሳሰሉትን ጉዳዮች የሚይዝ ነው፡፡
- መብትና ግዴታ፤
የንግድ ሥራ ፈቃድ አጠቃቀምን አስመልክቶ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 የተለያዩ ድንጋጌዎችን አስቀምጧል፡፡ የንግድ ፈቃድ ያለው ሰው በሕግ የተሰጡት መብቶች ያሉትን ያህል ግዴታዎችም አሉት፡፡ ከእነዚህ ግዴታዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የንግድ ሥራ ፈቃድ በስሙ የተሰጠው ሰው/ድርጅት ፈቃዱን ለተሰጠው የንግድ ሥራ መስሪያ ብቻ እንዲውል የማድረግ ግዴታ አለበት፤ በሌላ አነጋገር ፈቃዱ ለተሰጠው ነጋዴ እና ለመነገድ ብቻ የሚያገለግል ግላዊ /personal document/ ሰነድ ነው፡፡ ስለሆነም የንግድ ሥራ ፈቃድ ከተሰጠበት ዓላማ ውጭ መገልገል፤ ለምሳሌ፡- ፈቃዱን ለሌላ ሰው ማከራየት፣ ማዋስ፣ በስጦታ፣ በመያዣነት ወይም በሌላ ማናቸውም አኳኋን ፈቃዱን አሳልፎ መስጠት አይፈቀድለትም፡፡
2. የንግድ ሥራ ፈቃድን በማከራየት ወይም በሌላ አኳኋን ከተሰጠበት ዓላማ ውጭ ሲገለገል የተገኘ ነጋዴ የሕግ ተጠያቂነቱ ምንድን ነው?
የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 የንግድ ሥራ ፈቃዱን ያከራየ፣ ያዋሰ ወይም በመያዣነት ሌላ ሰው እንዲገለገልበት አሳልፎ የሰጠ መሆኑ ሲረጋገጥ አስተዳደደራዊ እና የወንጀል ተጠያቂነቶችን ያስከትልበታል፡፡ አስተዳደራዊ ተጠያቂነቱ ንግድን በሚመራውና በሚመራው የንግድ ሚኒስቴር ወይም የንግድ ቢሮ ወይም በሌላ ፈቃድ ሰጪ አካል በነጋዴው ላይ የሚተላለፍ እርምጃ ሲሆን በዚህም መሰረት የመጀመሪያው የንግድ ሥራ ፈቃድ እገዳ (አንቀጽ (29)(1) (ሠ) ይመልከቱ) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የንግድ ሥራ ፈቃድ ስረዛ ነው (አንቀጽ (30(1)(ሐ) ይመልከቱ)፡፡
ሌላኛው ተጠያቂነት ደግሞ የወንጀል ኃላፊነት ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሰውን ተግባር የፈጸመ ነጋዴ ከብር 50,000 እስከ ብር 100,000 በሚደርስ የገንዘብ መቀጫ እና ከ5 ዓመት እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል (አንቀጽ 49(4)ን ይመልከቱ)፡፡ ነጋዴው የውጭ አገር ዜጋ ሲሆን ደግሞ ቅጣቱ ከፍ ብሎ ከብር 200,000 እስከ ብር 300,000 በሚደርስ የገንዘብ መቀጫና ከ7 ዓመት - 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡
3. የንግድ ፈቃድን ተከራይቶ የሚሰራ ሰው ያለበት የሕግ ተጠያቂነት ምንድን ነው?
ቀደም ሲል እንደገለጽነው ማንኛውም ሰው የንግድ ሥራን ለመስራት አስቀድሞ ሕጋዊ የሆነ የጸና የንግድ ሥራ ፈቃድ መያዝ ይኖርበታል፡፡ አንድ የንግድ ሥራ ፈቃድ ለአንድ ነጋዴ ብቻ የሚያገለግል ግላዊ ፈቃድ ነው፡፡ ስለሆነም ግለሰቡ የሌላ ሰውን የንግድ ሥራ ፈቃድ በኪራይ በመያዝ የንግድ ሥራ እያከናወነ ቢገኝ ያለንግድ ፈቃድ የንግድ ሥራ እያከናወነ እንዳለ ይቆጠራል ማለት ነው፡፡ ይህም ደግሞ አስተዳደራዊና የወንጀል ተጠያቂነቶችን ያስከትልበታል፡፡ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁ አንቀጽ 49(2) የጸና የንግድ ሥራ ፈቃድ ሳይኖረው እየነገደ የተገኘ ሰው የንግድ ሥራ ሲካሄድባቸው የነበሩ የንግድ ዕቃዎች እና የአገልግሎት መስጫና የማምረቻ መሳሪያዎች መወረሳቸው እንደተጠበቁ ሆነው ከብር 150,000 እስከ ብር 300,000 በሚደርስ መቀጫ እና ከ 7 ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚቀጣ ይሆናል ማለት ነው፡፡
GMS law office !