25/05/2026
ከ418 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው በይፋ ተመረቁ
---------------------------------
ሰንበቴ:ግንቦት 17/2018 ዓ.ም(ጅሌ ጥሙጋ ኮሙኒኬሽን)
በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖራቸዋል የተባሉና ከ418 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የተለያዩ የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ዛሬ ተመርቀዋል።
ከ2013 እስከ 2014 ዓ.ም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በወረዳው በደረሰ ውድመት የወረዳው ማህበረሰብ ለዓመታት ለከፋ እንግልት እና ስቃይ ተዳርጎ መቆየቱ ይታወሳል።
በዚህም በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ የ3R ፕሮጀክት ከ418 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ የወደሙ ተቋማትን መልሶ በመገንባት በ19 ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ 75 የልማት ፕሮጀክቶችን ለምረቃ አብቅቷል።
ፕሮጀክቱ ላለፉት አንድ አመት 23 የትምህርት፣ 10 የጤና እና 42 የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት በተለያዮ ቀበሌዎች ለመገንባት በእቅድ ሲሰራ ቆይቷል።
በትምህርት ዘርፍ በተከናወነው መልሶ ግንባታ አንድ የተማሪዎች ቤተ-መጻሕፍት እና በተለያዩ ቀበሌዎች 22 የመማሪያ ክፍሎች፣እንዲሁም በጤናው ዘርፍም የማህበረሰቡን የህክምና እንግልት በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ የሚያስችሉ ደረጃቸውን የጠበቁ ጤና ኬላዎች። በተያያዘም በተለያዮ ቀበሌዎች 38 የመጠጥ ውሃ ተቋማትን ግንባታ በእለቱ በይፋ ተመርቀዋል።
ከ3R ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በበጀት ዓመቱ በመደበኛ በጀት የመንገድ ግንባታ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ የሚውሉ የሼድ ግንባታዎች እንዲሁም በዋሽ (WASH) ፕሮጀክት አማካኝነት የተለያዩ የልማት ስራዎችም መመረቃቸው ነው የተገለጸው።
በምረቃው መርሃ-ግብር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ሰይድ በግጭቱ ምክንያት የወደሙ መሠረተ-ልማቶች በማህበረሰቡ ላይ ያደረሱት ስቃይና እንግልት ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ የ 3R ፕሮጀክት ባደረገው ከፍተኛ ድጋፍና ርብርብ የወደሙ የትምህርት፣ የጤና እና የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት መገንባታቸው በወረዳው በተደጋጋሚ ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ የሰጠ መሆኑን አቶ አሊ ተናግረዋል።በመሆኑም ለፕሮጀክቱ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት በሙሉ በወረዳ አስተዳደሩ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ አባአፍሮ በበኩላቸው መንግስት በግጭት ሳቢያ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም እና ልማትን ለማስቀጠል በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።አያይዘውም የ 3R ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን የመሰለ ሰፊ ተደራሽነት ያለው የመልሶ ግንባታ ስራ ማጠናቀቁ ለቀጣይ የልማት ስራዎች አቅም የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው የተገነቡት የልማት ተቋማትን ህብረተሰቡ ጥበቃና እንክብካቤ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ በጥብቅ አሳስበዋል።
ለዓመታት በንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት እና በጤና ተቋማት መውደም ምክንያት ከፍተኛ ስቃይና እንግልት ውስጥ ነበርን ሲሉ ተሳታፊዎች በውይይት ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን አሁን ግን ተቋማቱ በመገንባቱ ደስታችን ወደር የለውም በማለት ገልጸዋል።
በመጨረሻም ለፕሮጀክቱ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የክልል ፕሮጀክት አስተባባሪዎች እና የስራ ኃላፊዎች፣ ለዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ ለፕሮጀክት አስተባባሪው እንዲሁም ፕሮጀክቱን በቅርበት ሲመሩ እና ሲደግፉ ለነበሩ አመራሮችና ባለሙያዎች የሚገባቸው እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።