የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ Bahir Dar cit Administration police

  • Home
  • Ethiopia
  • Bahir Dar
  • የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ Bahir Dar cit Administration police
14/09/2026
12/09/2026

የ2019 አዲስ ዓመት በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም ተጠናቋል።

የ2019 አዲስ ዓመት በዓል በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ያለምንም የፀጥታ ችግር በሙሉ ሰላም እና ደስታ ተከብሮ መጠናቀቁን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል አበበ ውቤ አስታወቁ።

ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል አበበ ውቤ እንደገለጹት፤ ህዝቡ አዲሱን ዓመት በሰላም እና በፍቅር ተቀብሎ እንዲያከብር አስቀድሞ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል እቅድ በመንደፍ ወደ ስራ ተገብቷል። በዚህም መላው የፀጥታ ኃይል ባደረገው የቅንጅት ስራ እና ባከናወነው የወንጀል መከላከል ግብረ-ኃይል እንቅስቃሴ በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ስጋት በሰላም ሊጠናቀቅ ችሏል።

በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታ ኃይሉ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጋና ያቀረቡት ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራሉ ህብረተሰቡም ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን ያደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍና ያሳየው ቀና ትብብር ለሰላሙ መረጋገጥ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በአዲሱ ዓመትም ከአካባቢው የፀጥታ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅትና አጋርነት አጠናክሮ በመቀጠል፣ ለሰላምና ደህንነት መረጋገጥ የሚጠበቅበትን የወንጀል ስጋቶችን የመጠቆም እና የመከላከል ሚና እንዲወጣ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል አበበ ውቤ ጥሪ አቅርበዋል።

10/09/2026

"የጸጥታ መዋቅሩ ሌሊት እና ቀን በመታገል ለሀገር ሰላምና አንድነት ያሳዩት ፅናትና ታማኝነት የሚበረታታ ነው!" ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለፌደራል ፖሊስ፣ ለክልሉ መደበኛና አድማ መከላከል ፖሊስ እንዲሁም ለሚሊሻ፣ ለሰላም አስካባሪ እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የ2019 የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልከተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አዛዡ በመልዕክታቸው እንደገለጹት ያለፈው ዓመት የህዝብን ሰላም፣ ደህንነትና ለማረጋገጥ በርካታ ፈተናዎችን በማለፍና ከባድ መስዋዕትነት በመክፈል ውጤት የተመዘገበበት ነበረ ብለዋል።

በተለይም የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልሉ መደበኛና አድማ መከላከል ፖሊስ፣ የሚሊሻ እና የሰላም አስካባሪ አካላት በጥብቅ ቅንጅት በመስራት የህግ የበላይነትን ለማስከበርና የህዝብን ሰላም ለማስጠበቅ ያደረጉትን ተጋድሎ አድንቀዋል።

የጸጥታ መዋቅሩ ሌሊት እና ቀን በመታገል ለሀገር ሰላምና አንድነት ያሳዩት ፅናትና ታማኝነት የሚበረታታ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ህዝቡ ከጸጥታ አካላት ጎን በመቆም፣ ድጋፍ በመስጠትና መረጃ በመስጠት ላሳየው ቀጣይነት ያለው አጋርነት በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።

አዲሱ የ2019 ዓ.ም የመቻቻል፣ የአንድነት፣ የልማትና ሙሉ ሰላም የሚሰፍንበት ዘመን እንዲሆን የጸጥታ አካላት ሰላምን የማስከበርና የማስጠበቅ ግዴታቸውን በተጠናከረ ወታደራዊና ፖሊሳዊ ስነ-ምግባር እንዲሁም በከፍተኛ ህዝባዊ ወገንተኝነት እንደሚወጡ ሌተናል ጀኔራል ጥጋቡ ይልማ አረጋግጠዋል።

ሰላም የሁላችንም የጋራ ሀብት በመሆኑ በአዲሱ ዓመትም የሰላም ጥበቃው ይበልጥ እንዲጠናከር የህዝቡ የጠበቀ አጋርነት እንዳይለይ አዛዡ ጥሪ አቅርበዋል።

በመጨረሻም አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ የፍቅርና የስኬት ዓመት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

07/09/2026

የ2019 አዲስ ዓመት በዓል በሙሉ ሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጎን እንዲሆን ጥሪ ቀርቧል።

የ2019 አዲስ ዓመት በዓል በፍጹም ሰላም እንዲከበር የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሰላም እና የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፏል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ መጪውን የ2019 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለፌደራል ፖሊስ፣ ለክልሉ የመደበኛ እና የአድማ ብተና ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለሰላም አስከባሪና ሚሊሻ ኃይሎች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

በዓሉ በፍጹም ሰላምና ደስታ ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ፣ አሽከርካሪዎች እና የንግዱ ማህበረሰብ አስፈላጊውን የጥንቃቄ እና የትብብር እርምጃ እንዲወስዱ ዋና ጠቅላይ መምሪያው ጥሪ አቅርቧል።

የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ እንደገለጹት በበዓል ወቅት የሚፈጸሙ የሰርጎ ገቦች እና የአጭበርባሪዎችን ሴራ ለመከላከል ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል።

ኃላፊው አክለውም ግብይቶች ህጋዊ ከሆኑ የገበያ ማዕከላት ብቻ መፈጸም እንዳለባቸው፣ ከአታላዮች ራስን መጠበቅ እንደሚገባ፣ ከተሰረቁ እንስሳት ግዢና ህገ-ወጥ የግብይት እንቅስቃሴዎች መራቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም በበዓል ወቅት ሊበራከቱ ከሚችሉ ሀሰተኛ የብር ኖቶች አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግና የተጠራጠሩትን የብር ኖት በአቅራቢያ ወደሚገኝ ባንክ በመውሰድ ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገልጿል። የሐሰተኛ ብር እና የሌብነት ስጋቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመቀነስም የሞባይል ባንኪንግ (Mobile Banking) እና ሌሎች ዲጂታል የክፍያ አማራጮችን መጠቀም እንደሚገባ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል የመንገድ ትራፊክ አደጋዎችን ለመከላከል እና የሰዎችን ህይወትና ንብረት ለመጠበቅ አሽከርካሪዎችና እግረኞች የትራፊክ ህጎችን በአግባቡ እንዲያከብሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አሽከርካሪዎች ፍጥነት በመቀነስና ህግን በማከበር የማሽከርከር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ በበዓል አጋጣሚ ከአቅም እና ከተወሰነው ታሪፍ በላይ ክፍያ ከማስከፈል እንዲቆጠቡ እንዲሁም አልኮል ጠጥቶ ማሽከርከር በሰው ህይወት ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትል በመሆኑ በፍጹም ከአልኮል መጠጥ በኋላ እንዳያሽከረክሩ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

ለአቅመ-ደካሞች፣ ለህፃናት እና ለእግረኞች ሁልጊዜ ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባና እግረኞችም የመንገዱን ግራ መስመር ይዘው በመጓዝ የትራፊክ አደጋ ስጋትን የመቀነስ ግዴታቸውን እንዲወጡ ኃላፊው አሳስበዋል።

በመኖሪያ ቤቶችና በተለያዩ የንግድ ተቋማት ውስጥ በሚደረግ የኤሌክትሪክ አጠቃቀም ላይ አስፈላጊው ጥንቃቄ ካልተደረገ ድንገተኛ የእሳት አደጋ ሊከሰትና በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል፣ ህብረተሰቡ ተገቢውን የቅድመ-ጥንቃቄ እርምጃ እንዲወስድ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ጠቁመዋል።

በዓሉ በሙሉ ሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጎን በመቆም በአካባቢው አጠራጣሪ ነገሮችን ወይም ሰዎችን ሲያይ ወዲያውኑ በአቅራቢያው ለሚገኝ የፖሊስ አካል ወይም በጥቆማ መስጫ መስመሮች ጥቆማ በመስጠትና ወንጀልን በጋራ የመከላከል ባህልን በማጠናከር ከፀጥታ ኃይሎች ጋር እንዲተባበር ጥሪ ቀርቧል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለመላው የሀገራችን ህዝብ የሰላም እና የደስታ የዘመን መለወጫ በዓል እንዲሆን ይመኛል!

Address

Bahir Dar

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ Bahir Dar cit Administration police posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Shortcuts

Share

Category