10/09/2026
"በአዲሱ ዓመት ከተማችን የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝምና የኢንዱስትሪ መዳረሻነቷ ይበልጥ የሚጎለብትበት፣ የተጀመሩ ታላላቅ የልማት ስራዎች ተጠናቀው ለህዝብ አገልግሎት የሚበቁበት፣ የአብሮነት፣ የመተሳሰብ እና የወንድማማችነት እሴቶቻችን የሚጠነክሩበት እንዲሆን እመኛለሁ"
ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝባችን እና ለውቢቷ ባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በሙሉ
በቅድሚያ እንኳን ከአሮጌው ዘመን ወደ አዲሱ የምስራች ዘመን በሰላም፣ በጤና እና በህይወት አሸጋገራችሁ! እንኳን ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! ፣ ዓመቱ የሠላም ፤የጤና ፤ የአንድነትና የእድገት እንዲሆንልን ምኞቴን መግለጽ እወዳለሁ፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ውብ ባህሎች፣ የከበሩ በዓላት እና የህብረ-ብሔራዊ አንድነት መገኛ ናት። የአዲስ ዓመት በዓል ደግሞ ሁሉም ሃይማኖቶች፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ማህበረሰቦች በአንድነት በፍቅርና በደስታ የሚያከብሩት ትልቅ የጋራ እሴታችን ነው። አዲስ ዘመን ሲመጣ ሁልጊዜም አዲስ ተስፋን፣ ፍቅርን፣ ሰላምንና ስኬትን ይዞልን እንደሚመጣ ሙሉ እምነት አለን።
ባሳለፍነው ዓመት የከተማችንን ሰላምና ፀጥታ ከማስከበር ጎን ለጎን፣ ውቢቷን ባህር ዳር ለነዋሪዎቿ፣ ለባለሀብቶችና ለቱሪስቶች ይበልጥ ማራኪና ምቹ ለማድረግ ከ 20 ሺ በላይ ዜጎች የቤት መስሪያ ቦታ፣ የኮሪደር ልማት እና የፅዳትና ውበት ስራዎችን በስኬት አከናውነናል። ይህ የተጀመረው የልማትና የስማርት ባህር ዳር ጉዞ፣ በአዲሱ ዓመትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
እነሆ ከፊታችን 365 ገጾች ያሉት አንድ ትልቅ መዝገብ ተከፍቷል፡፡ ምንም አልተጻፈበትም፡፡ በዚህ መዝገብ ላይ የኢትዮጵያን ብልጽግና እንጻፍበት፡፡ እኛ የኢትዮጵያን ብልጽግና ካልጻፍንበት ሌሎች የኢትዮጵያን ድካም ይጽፉበታል፡፡ መሽቀዳደም አለብን፡፡ እሽቅድድሙ ከጊዜ ጋር ነው፡፡ ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ጋር ነው፡፡
በመጨረሻም
በአዲሱ ዓመት ሁላችንም በአንድነት እና በሕብረት በመቆም ለመጭው ትውልድ መልካም ነገር በመስራት ከተረጀነት ወደ ምርታማነት የምንሸጋገርበት የስኬት እና የብልጽግና ዓመት ይሆን ዘንድ ከልብ እመኛለሁ ፡፡
በድጋሚ እንኳን ለ2019 አዲስ አመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ ፤ አደረሰን
መልካም አዲስ ዓመት!
ጉሹ እንዳላማው
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ