30/05/2026
የወተት ምርትን በዘመናዊ የባዮቴክኖሎጂ ዘዴ ለማሳደግ የሚያስችል «ሞዴል የወተት መንደር» ምስረታ ስራ መጀመሩ ይፋ ሆነ!
በክልል ካፒታል በጀት እና በብሄራዊ እንስሳት ባዮቴክኖሎጂ ምርምር ፕሮግራም የበጀት ድጋፍ የወተት ምርታማነትን በማሳደግ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል፣ መንደር መሰረት ያደረገ የዝርያ ማሻሻል ስራ መጀመሩ ይፋ ተደርጓል። በአንጎለላና ጠራ ወረዳ ጨኪ ቀበሌ የተጀመረው ይህ በምርምር ላይ የተመሰረተ የዝርያ ማሻሻል ስራ፤ በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ስር በሚገኘው የደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል እና በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ስር በሚገኘው የቢሾፍቱ ግብርና ምርምር ማዕከል ጥምረት የሚከናወን ነው።
የደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል እንስሳት ቴክኖሎጂ አቅርቦት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የማዕከሉ ተወካይ አቶ ልዑልሰገድ አለማየሁ እንደገለጹት፤ ስራው የላሞች ልየታን፣ ስልጠናን እና ቋሚ የወተት መንደር ምስረታን በማካተት ለሌሎች አካባቢዎች ሞዴልና ማስተማሪያ እንዲሆን ታስቦ የተጀመረ መሆኑን ተናግረዋል። የአንጎለላና ጠራ ወረዳ ተወካይ አቶ በሻህ አጉኔ በበኩላቸው፤ አርሶ አደሩ ይህንን ቴክኖሎጂ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ምርታማነቱን ሊያሳድግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ይህ በእንስሳት ባዮቴክኖሎጂ ምርምር ዘርፍ የተጀመረው ስራ በተመሳሳይ ጊዜ ወደ ድሪ (Estrus Synchronization) እንዲመጡ እና ፆታው በተለየ የኮርማ ዘር (Sexed Semen) የሰው ሰራሽ ማዳቀል ቴክኖሎጂዎችን በማቀናጀት ጥቅም ላይ የሚያውል ነው። ቴክኖሎጂው በተለይ እስከ 90 በመቶ የሚደርሱ ሴት ጥጃዎችን ለማግኘት ማስቻሉ፣ የበሽታ ስርጭትን መቀነሱ እና የመተኪያ ላሞችን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ለመቆጣጠር መርዳቱ ዋነኛ ጥቅሞቹ እንደሆኑ ተገልጿል።
የሰው ሰራሽ ማዳቀል (AI) ስራ ቆየት ያለ ቢሆንም፣ ከአጠቃቀም ችግሮች ጋር ተያይዞ የሚጠበቀውን ያህል ውጤት እንዳልተገኘበት በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ቢሾፍቱ ግብርና ምርምር ማዕከል ተመራማሪና እንስሳት ባዮቴክኖሎጂ ምርምር ፕሮግራም ብሔራዊ አስተባባሪ ዶ/ር ሰይድ አሊ አስታውሰዋል። በቢሾፍቱ አካባቢ ይህንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ጥሩ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው መንደርን መሰረት በማድረግ የዚህን አካባቢ አ/አደር ተጠቃሚ እንዲሆን እንሰራለን ብለዋል። ለውጤታማነቱም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል ።
የማዕከሉ የእንስሳት ጤና ተመራማሪው ዶ/ር ቸኮል ደምስ በበኩላቸው፣ ሁሉም እንስሳት በአንዴ ለቴክኖሎጂው ብቁ ላይሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመው፤ ለቀጣይ ብቁ እንዲሆኑ በአመጋገብና በጤና አያያዝ እንዲሻሻሉ ተደርገው እንደሚመረጡ ገልጸዋል። በመሆኑም አርሶ አደሮች የመመረጣቸውን ዕድል በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባና ቋሚና ሞዴል የወተት መንደር ለመመስረት የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም ተናግረዋል። የሚወለዱት ጥጆች ሴት መሆናቸው ትልቅ ጥቅም እንዳለውም አብራርተዋል።
በዚሁ የቴክኖሎጂ ትግበራ/ሽግግር ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የደብረ ብርሃንና የቢሾፍቱ ግብርና ምርምር ማዕከላት ተመራማሪዎች፣ የሰሜን ሸዋ ዞን እንዲሁም የአንጎለላና ጠራ ወረዳ የእንስሳትና ዓሳ ሀብት መምሪያና ጽህፈት ቤት ባለሙያዎችና የአካባቢው አርሶ አደሮች በጋራ ተገኝተዋል።
አማራጭ የመረጃ ምንጮቻችን ይወዳጁ
Telegram
https://t.me/dbarc_2016
Youtube
https://youtube.com/?si=K-4ZMq86IVQiP_Eo
Facebook
https://www.facebook.com/share/16kWNBZdYE
LinkedIn
https://www.linkedin.com/.../debre-birhan-agricultural.../