20/05/2026
ፍትሕ፣ ርኅራኄና መጠለያ በአል-ነጃሺ ምድር
አል-ነጃሺ መስጊድን ማየት የሰው ልጅ በጭንቅና በጨለማ ውስጥ በነበረበት ዘመን እምነትና ፍትሕ፣ ርኅራኄና መጠለያ በአንድ ወርቃማ መሠረት ላይ እንዴት ፍጹም ተጋብተው እንደኖሩ በጥልቀት መመልከት ነው። ይህ በዓለም ታሪክ ውስጥ ፈጽሞ የማይረሳውና በጥንታዊው የነጋሽ ምድር የሰፈረው ቅዱስ ስፍራ የሕንጻ ስብስብ አይደለም። እርሱ የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች የነፃነትና የሥነ-ልቦና ደኅንነት እስትንፋስ ያገኙበትና የኢትዮጵያዊው ንጉሥ የአል-ነጃሺ (አሥሐማ ኢብን አብጀር) የላቀ የሞራል ልዕልና የታተመበት እና የሰው ልጅ የጋራ የክብር ማኅተም የሆነ ሕያው የተቋማዊ ጽናት ሐውልት እንጂ። የነጃሺ ታሪክ የስደት ሰቆቃ በጥልቅ ፍቅር፣ በፍትሕና በሉዓላዊ ውህደት የተሻረበት ነፍስን የሚያሞቅ ቅኔ ነው።
የዚህ ታላቅ ታሪክ የሕይወት ቅኝት የሚጀምረው በነብዩ መሐመድ አንደበት ከተነገረችው ያቺ ዘላለማዊ የእውነት ምስክርነትና ስልታዊ ማኅደረ-ትውስታ ነው። በመካ ምድር እምነታቸውን በመያዛቸው ብቻ ስቃይና መከራ፣ ብርቱ ተቃወሞም የጸናባቸው ሰሃቦች መጠለያ ፍለጋ ሲጨንቃቸው ነቢዩ መሐመድ ጣታቸውን ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ወደ ሐበሻ ምድር በመቀሰር እንዲህ አሉ፦ “ወደ ሐበሻ ምድር ሂዱ እዚያ ዘንድ ማንም የማይበደልበት፣ ፍትሕንና እውነትን የሚወድ ንጉሥ አለና።” ይህች ቃል ተራ መመሪያ አልነበረችም የኢትዮጵያን ጥንታዊ የፍትሕ፣ የባለደራነት ክብርና ሉዓላዊነት ለዓለም ያበሰረች፣ በሰማይና በምድር የተመሰከረች የቃል-ኪዳን ብርሃን እንጂ።
ይህ የፍትሕ ልዕልናና ስልታዊ ትሕትና በነጃሺ አደባባይ በተግባር ሲገለጥ ታሪኩ ይበልጥ ድንቅ ተቋማዊ ትምህርት ሰጪ ይሆናል። በጃዕፈር ኢብን አቢ ጣሊብ የሚመራው የስደተኞቹ ስብስብ በንጉሡ ፊት በቆመበትና የመካው ጃዕፈር የቁርዓን አንቀጾች በጥንቃቄ ባነበበበት ያ ታሪካዊ ቅጽበት የነጃሺ ልብ በፍቅርና በእውነት ጸና። ንጉሡ አል-ነጃሺ ከመንበሩ ወርዶ በትሕትና ምድር ላይ መስመር እየሳለ እንዲህ አለ፦ “በእኛና በእናንተ እምነት መካከል ያለው ልዩነት ከዚች መስመር አይበልጥም፤ በምድሬ ላይ በሰላምና በነፃነት ኑሩ።” የመካ መሪዎች ወርቅና የከበሩ ስጦታዎችን ይዘው ስደተኞቹን አሳልፎ እንዲሰጣቸው ቢማጸኑትም ንጉሡ ግን ወርቁንና ጉቦውን ትተው የሞራልና የፍትሕ ዙፋን ከማናቸውም ምድራዊ ጥቅም በላይ መሆኑን አስመሰከረ።
የነጃሺን ታሪክ ይበልጥ ረቂቅና የማይረሳ የሚያደርገው በማኅበረሰቡ ውስጥ ያስቀመጠው ጥልቅ የአንድነትና የመከባበር ቃል-ኪዳን ነው። አል-ነጃሺ መስጊድ የጥንታዊ ሥልጣኔ አሻራ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ለሰው ልጅ ክብርና ለሥነ-ልቦና ደኅንነት የሰጡትን ታላቅ ዋጋ የሚያሳይ ሕያው ምስክር ነው። በዚያው ቅዱስ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያረፉት የሰሃቦች መቃብርና የነጃሺ ራሱ የክብር ታሪክ ዛሬም ድረስ በነጋሽ አየር ውስጥ ፍቅርንና ሰላምን እየረጨ ያልፋል። ይህ ታሪክ ያስተማረን ትልቁ ምስጢር እውነተኛ እምነትና ሰብዓዊነት የሚለኩት በሰው ልጅ ላይ በሚደረግ ርኅራኄ የተሰደደውን በፍቅር በማቀፍና ለፍትሕ በጽናት በመቆም መሆኑን ነው።
ከታሪካዊው አል-ነጃሺ መስጊድ የሚሰማው የአዛን ወይም የጸሎት ድምፅ ከተፈጥሮው ጸጥታና እርጋታ ጋር ሲቀላቀል በሰው ነፍስ ውስጥ የማይጠፋ መንፈሳዊ እርካታን ይፈጥራል። ያ ውብ ዜማ የጥንቱን ፍትሕ ያስታውሳል፣ የነገውን የሰላምና የአንድነት ራዕይ ያቀጣጥላል ጥንታዊው የሐበሻ ደግነትና የንቃት አቅም ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፍ በየቀኑ ይመሰክራል። ነጃሺና የመጀመሪያው ሂጅራ ማለት ፍትሕ መልክ አውጥቶ፣ ርኅራኄና እንግዳ ተቀባይነት አካል ገዝቶ፣ የሰው ልጅ እውነተኛ ክብር በምድር ላይ ሲታተም የታየበት ሕያው ተአምር ነው።
ዛዲግ አብርሃ
የአፍሌክስ ፕሬዝደንት