17/07/2026
በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ343 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተጠናክሮ ሊቀጥሉ ይገባል። አቶ አይሶፄ ሂሎታ
የአርባምንጭ ከተማ የክረምት በጎ አብይ ኮሚቴ የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ ተግባራት አፈጻጸም ሪፖርትን ገመገመ፡፡
አብይ ኮሚቴው የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ ከሚመለከታቸው የሴክተር ኃላፊዎች ጋር በመሆን ታቅደው የተከናወኑ ተግባራትን መነሻ በማድረግ አፈጻጸሙን ገምግመዋል፡፡
የዘንድሮው የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በሚያስችሉ 18 ዘርፎች ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡
በመድረኩ ላይ የአርባምንጭ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ እና የአቢይ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አይሶፄ ሂሎታ እንደገለጹት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዕቅድ በማቀድ አፈጻጸሙን እየገመገሙ መምራትና ተግባሩን ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዘንድሮው የክረምት መርሃ ግብሩ 62 ሺህ ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ላይ በንቃት በማሳተፍ 343 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክሮ ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
በበጎ ተግባር በርካታ አካላትን በማሳተፍ የእነዚህን አቅማቸውን በማቀናጀት በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ችግር ለመፍታት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
አቶ አይሶጼ አክለውም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን ማጠናከር፣ በበጎ ተግባራት የሚሳተፉ አካላትና ማህበራትን ማሳተፍ፣ የክረምት ትምህርት ተግባር ማጠናከር፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት ግንባታ ማድረግ ስራዎችንና ሌሎችን በልዩ ትኩረትና ቅንነት መፈጸም ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊና የክረምት በጎ ፈቃድ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሀብታሙ አበራ እንደተናገሩት የ2018 በጀት ዓመት የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን በቅንጅት በመስራት የታለመለትን ግብ ለማሳካት ሁሉም የኮሚቴ አባላት ከዕቅድ እስከ ትግበራ ድረስ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይጠበቃል ብለዋል።
በ2017 ዓ/ም ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡ የተገለጸ ሲሆን በ2018 ዓ/ም ከተጀመረ በ15 ቀናት ውስጥ የተከናወኑ ተግባራት የደም ልገሳ፣ቤት ግንባታ ማስጀመሪያ፣ትምህርትና ስልጠና፣የችግኝ ተከላ መርሃግብር እና ሌሎች መካሄዱ በሪፖርቱ ተጠቅሷል
በመድረኩ በክረምት በጎ እየተከናወኑ ያሉ የተግባር አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ አፈጻጸሙን መነሻ በማድረግ ግምገማ ተደርጓል፡፡
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ኮሚቴው በከተማው የሚገኙ ወጣቶች፣ ባለሀብቶችና አጠቃላይ ማህበረሰቡ በበጎ ፈቃድ ሥራዎች ላይ በንቃትና በባለቤትነት ስሜት እንዲሳተፉ በማድረግ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገልጿል።
ኮሚቴው በተለያዩ ስራ ዘርፎች የተከናወኑ የእስካሁኑ ተግባራትን በጥልቀት ከገመገሙ በኃላ ቀጣይ ተግባራትን ስኬታማ ማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በአሰፋ ጪሻ