03/06/2026
የዓለም የአካባቢ ቀን በሀገራችን ግንቦት 28/2018 በተለያዩ ኩነቶች ይከበራል።
ግንቦት 27/2018
አዲስ አበባ
============
የዓለም የአካባቢ ቀን በየዓመቱ ግንቦት 28 ይከበራል፡፡ የዘንድሮ የዓለም አካባቢ ቀን “Climate Action’’ በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ53ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ይከበራል።
የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ሁኔታ እና የበአሉ አስፈላጊነትን በተመለከተም ሀገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት የምታበረክተው አስተዋጽኦ ከ 0.5% በታች ቢሆንም፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለሚከሰቱት ተደጋጋሚ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተት፣ የደን መመናመንና የመሬት መራቆት በእጅጉ ተጋላጭ ናት። እነዚህ ተግዳሮቶች በዝናብ ጥገኛ በሆነው ግብርና፣ በምግብ ዋስትና፣ በውሃ ሀብታችን እና በገጠሩ ማኅበረሰብ የኑሮ ሁኔታ ላይ ቀጥተኛ ስጋት ደቅነዋል። በመሆኑም “Climate Action’’የሚለው መሪ ቃል ለኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም ያለው። የአገራችን አየር ንብረት ለውጥ ምላሽ በሚከተሉት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትክረት በማድረግ እየተሰሩ ይገኛሉ፦
የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር፦ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋኑን ወደ 23.6% አሳድጋለች።
የ2018 ዓ.ም ትኩረታችን የችግኞችን የመጽደቅ መጠን ማሻሻል፣ ዘላቂ የተፋሰስ ልማት እና የረጅም ጊዜ ሥነ-ምህዳራዊ ጥቅሞችን ማረጋገጥ ላይ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ግብርና እና የውሃ ልማት፦ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወደ አፈር ጥበቃ፣ መስኖ ማስፋፋት እና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም (climate-smart) አሠራሮች መሸጋገር።
ወደ አረንጓዴ ኢነርጂ/የሐይል ምንጭ ሽግግር፦ ከ95% በላይ ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ስኬታችንን መሰረት በማድረግ፣ ንጹህ ኃይልን ወደ ትራንስፖርት እና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማስፋፋት።
የከተሞች ጽዳትና ውበት፦ የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ እና የከተማ አረንጓዴ መሠረተ-ልማትን ማጠናከር እና ከከተሞች የሚወጣውን የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት በመቀነስ።
ለአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ፋይናንስ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለእውቀት ማሳደግ አጋርነትን ማጠናከር።
የዘንድሮ የዓለም አካባቢ ቀን ሲከበርም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንዲሁም መላው የህብረተሰብ ክፍል የሚከተሉትን ተግባራት ከግምት ውስጥ በማስገባት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ችግኞችን መትከል እና መንከባከብ።
ዘላቂ የቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ ሥርዓትን መከተል።
የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄን ላይ በንቃት መሳተፍ።
ለረጅም ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ እና የሚበሰብሱ የእቃ መያዣዎችን በመጠቀም፡፡
ለአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ፋይናንስ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለእውቀት ማሳደግ አጋርነትን ማጠናከር።
የአካባቢ ጥበቃ እና እንክብካቤ ግንዛቤዎችን ማስፋፋት፡፡
በወንዝ ዳርቻ ልማት እና በኮሪዶር ማስፋፊያ ስራዎች የተገኙ ውጠየቶችን ለመጠበቅ እና ለማስፋት በሚደረግ ርብርብ ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን
ጽዱ ኢትዮጵያ ባህል እናደርግ