18/02/2026
ለውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ብቁ የሚያደርጉ መስፈርቶች ምን ምን ናቸው?
አዋጁ ምን ይላል?
ክፍል ስድስት
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዜጎች በዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ ያላቸውን ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥና መብታቸውን ለማስከበር ስልጠናንና የብቃት ማረጋገጫ ሥርዓትን ዋነኛ መሣሪያው አድርጓል።
በዚህ ክፍል ላይ በአዲሱ አዋጅ የተቀመጡት አራት መሠረታዊ የብቃት መስፈርቶች የሚከተሉት ናቸው፦
📍የትምህርትና የቋንቋ ዝግጁነት
✅ማንኛውም በውጭ ሀገር ለሥራ የሚሰማራ ዜጋ፣ የሚሰማራበት የሥራ መስክ የሚጠይቀውን መሠረታዊ እውቀትና ክህሎት መያዝ ይኖርበታል።
✅ከዚህ ባለፈም የሠራተኛውን መብት ለማስከበር የመጀመሪያው እርምጃ የሥራ ውልን መረዳት በመሆኑ፤ ሠራተኛው ቢያንስ በሚረዳው ቋንቋ የሚዘጋጀውን ውል አንብቦ የመረዳት አቅም ሊኖረው እንደሚገባ አዋጁ በግልጽ ይደነግጋል።
📍የሙያ ብቃት
✅በውጭ ሀገር የሚሰማራ ማንኛውም ሠራተኛ በትምህርት፣ በሥልጠና ወይም በተግባር ያገኘውን እውቀትና ክህሎት አግባብነት ካለው የትምህርት ተቋም ወይም የምዘና ማዕከል በተሰጠ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ ማረጋገጥ ይኖርበታል።
📍ተመላሾች
✅በአዲሱ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አዋጅ በውጭ ሀገር ሲሠሩ ቆይተው ወደ ሀገር የተመለሱ ዜጎች በሰሩበት የሥራ መስክ ድጋሚ መሰማራት ቢፈልጉ፣ የክለሳ ሥልጠና ወስደው አግባብ ባለው የምዘና ማዕከል የተሰጠ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ ከያዘ ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ ለመሥራት ብቁ ይሆናል፡፡
✅ነገር ግን ከዚህ ቀደም ከሚሰሩበት የሥራ መስክ መቀየር ከፈለጉ እንደ አዲስ ሥልጠና ወስደው ብቃታቸውን በምዘና ማረጋገጥ እንዳለባቸው አዋጁ ያስገድዳል።
📍የጤና ምርመራ
✅የጤና ምርመራ የሚከናወነው በጤና ሚኒስቴር እና እንደ አስፈላጊነቱ በመዳረሻ ሀገራት በጋራ በሚመርጡና ጥራታቸው በተረጋገጠ የጤና ተቋማት ብቻ ይሆናል።
✅የጤና ምርመራው የሚከናወነውም ሠራተኛው አሠሪው የሚጠይቃቸውን ሌሎች የብቃት መስፈርቶች ማሟላቱ ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ አዋጁ ይደነግጋል።
📍ሕጋዊ የጉዞ ሰነዶች
✅ማንኛውም ስምሪት በሕጋዊ መንገድ እንዲከናወን አስፈላጊው የጉዞ ሰነዶች ማጣራት ሂደት በሚኒስቴሩ በኩል ይከናወናል።
✅ለውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ጉዞ የሚያስፈልጉ ሰነዶች እንደ ጉዳዩ አግባብነት በኤጀንሲው ወይም በሠራተኛው አማካኝነት ለሚኒስቴሩ ይቀርባሉ።
✅ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዜጎች ደህንነቱ የተጠበቀ ጉዞ እንዲያደርጉ ለማስቻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሠራል።