12/08/2025
የሎተሪ ሥራ የህግ ሽፋን በኢትዮጵያ
መግቢያ
የሎተሪ ጨዋታ ከጥንት ማህበረሰብ ጀምሮ እንደመዝናኛ ወይም የእድል መሞከሪያ ሆኖ ጥቅም ላይ ሲውል የኖረ ነው። በተለይም በጥንታዊ ሥርዓቶች ውስጥ የነበሩ የንጉሳዊ ቤተሰቦች እንደ እጣፈንታ መወሰኛ ወይም በአንዳንድ ሁኔታዎች የኃይል ማሳያነት ሲጠቀሙበት የኖረ (የቆየ) የጨዋታ አይነት ነው። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የሎተሪ ንግድ እንደ አንድ የኢኮኖሚ ዘርፍ ተቆጥሮ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት በድንበር ተሻጋሪነትም (Site-Based) ሆነው ጭምር የሚሰሩት በኢንቨስትመንት ደረጃነት አድጓል። በኢትዮጵያ የሎተሪ እጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ገበያ ላይ የዋለው በ1954 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለ-ሥላሴ ዘመን ነበር። ከዚህ ጊዜ በኋላ በቅርፅ፣ በሽልማት መጠንና በአደረጃጀት እያደገ መጥቶ በብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ስር በሚዘጋጁት ሎተሪዎች እንኳ በአሁኑ ሰዓት እስከ 50,000,000 (ሃምሳ ሚሊዮን) የሚደርስ የገንዘብ ሽልማት መጠን ያላቸው ሎተሪዎች በገበያ ላይ ይገኛሉ።
በተለይ አሁን አሁን ከቴክኖሎጅ እድገትና የዲጂታል ገበያው መስፋት ጋር በተያያዘ የሎተሪ አጨዋወቱ ዘዴም በፍጥነት በመዘመን ላይ የሚገኝ ሲሆን ለምሳሌም አንዳንድ ድርጅቶች ከአካላዊ ውርርድ እስከ አጭር የፅሁፍ መልዕክት፣ ዌብሳይት፣ መተግበሪያዎችና መሰል ዘዴዎችን በመጠቀም የሎተሪ እጣዎችን የሚሸጡበት ወይንም ውርርዶችን የሚያካሂዱበትን ሁኔታ እናስተውላለን። በዚህ አጭር ፅሁፍ ስለሎተሪና ውርርዶች ምንነት፣ የህግ መሠረት፣ የአሰራር ቅድመ ሁኔታዎችና መስፈርቱን አሟልቶ አለመስራት ሊያስከትል ስለሚችለው የህግ ተጠያቂነት ተዳሷል።
ሎተሪ ምንድነው ?
ሎተሪ ቃሉ የእንግሊዝኛ ሲሆን በሀገራችንም እንዳለ ተወስዶ ለቃሉ የህግና የመዝገበ-ቃላት ፍች ተሰጥቶት እናገኛለን። ለዚህም እንደምሳሌ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ኢንስቲትዩት ያሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ሎተሪ የሚለውን ቃል “ተከታታይ ቁጥሮች የተሰጧቸው ብዙ ትኬቶች ለሰዎች ከተሸጡ በኋላ እጣ በመጣል አሸናፊ ለሆነው ቁጥር የተወሰነለትን ገንዘብ… እቃ በመስጠት የሚካሄድ ተግባር ነው” የሚል ፍች ሰጥቶታል። በሌላ በኩል የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደርን እንደገና ለማቋቋም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው ደንብ ቁጥር 160/2001 አንቀፅ 2(1) መሠረት “ሎተሪ” ማለት የሽልማት አሸናፊው በእድል በእጣ አወጣጥ ወይም በማንኛውም ሌላ ዘዴ የሚታወቅበት ጨዋታ ወይም ድርጊት ሲሆን ቶምቦላን ወይም ራፍልን፣ ሎቶን፣ ቶቶን፣ ፈጣን ሎተሪን፣ የቁጥር ሎተሪን የተደራራቢ ሽልማት ሎተሪን፣ የፕሮሞሽን ሎተሪን፣ ቢንጎን፣ የስፖርት ውርርድ ሎተሪንና ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊቶችን ይጨምራል። በአጠቃላይ ደንቡ ከመውጣቱ በፊት በስራ ላይ በነበረው አዋጅ ቁጥር 535/1999 ስር ተካተው የነበሩ ከአስር በላይ የሚሆኑ ልዩ ልዩ የሎተሪ አይነቶችን ከነትርጓሜያቸው እንዲቀጥሉ አድርጓል። በዚህም አሁን ላይ አንዳንዶችን በሁለት ጎራ ከፍሎ የሚያከራክረውን የስፖርት ውርርድ (ለጊዜው በአዲስ አበባ ደረጃ የተከለከለ) ጨምሮ በአጭር የፅሁፍ መልዕክት፣ በመተግበሪያዎችና በዌብ ሥርዓት የሚደረጉትን እንዲሁም ወደፊት ሊጨመሩ የሚችሉ መሰል የእጣ ውርርዶችን ሊጨምር የሚችል ሰፊ ትርጓሜ ነው።
በሎተሪ ሥራ ለመሰማራት መሟላት ያለባቸው ቅድመ-ሁኔታዎች
በደንቡ አንቀፅ 2(13) ስር የሎተሪ ሥራ ምንነትን አስመልክቶ የተቀመጠውን ትርጓሜ ስንመለከት፣ የሎተሪ ስራ ማለት ‘በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ማንኛውንም ሎተሪ በማዘጋጀት በሀገር ውስጥ መሸጥ፣ ማከፋፈል፣ ማጫወትና እጣ ማውጣት ወይም ሌላ ተመሳሳይ ተግባራት ማከናወን ነው በሚል ሰፍሯል። በዚህ መሠረት ማንኛውም አካል፣ ግለሰብ ይሁን ድርጅት እነዚህን በመሰሉ የሎተሪ ሥራ ተግባራት ላይ ለመሰማራት በዚህ ደንብ አንቀፅ 12 ጀምሮ በዝርዝር የሰፈሩትን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላትና ማክበር እንዳለበት ተመላክቷል። ከእነዚህ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታዎች መካከልም፣-
የሎተሪ ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ከብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር የተሰጠ የፀና ፈቃድ፣
በሎተሪ ሥራ ለመሰማራት በአዋጁ በግለሰብ ወይንም ከመንግስት ጋራ በጣምራ ሊሰራ የሚችል መሆኑን መለየት፣
ተገቢ ክልከላዎችን ማክበር፣ (ዝቅ ብሎ እንደተመላከተው)
ፈቃዱ የህዝብን ሠላምና ፀጥታ ወይም የሀገሪቱን ደህንነት የሚጎዳ የወንጀል ተግባር ላይ እንዳይውል የማድረግ ግዴታ
እንዲሁም በወንጀል አስቀጭ ተብለው ከተዘረዘሩ ተግባራት በመቆጠብ የሎተሪ ሥራን በህጋዊ መንገድ ማካሄድ የሚሉት ይገኙበታል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም በደንቡ አንቀፅ 2(5፣6፣7፣8፣9 እና 110) ስር የሰፈሩት ማለትም፣-ቶቶ፣ ፈጣን ሎተሪ፣ የቁጥር ሎተሪ፣ የተደራራቢ ሽልማት ሎተሪ እና ዘመናዊ የቢንጎ ሎተሪን በአስተዳደሩ ብቻ የሚካሄዱ በመሆናቸው ምክንያት ግለሰብ ወይም የግል ድርጅት በእነዚህ የሎተሪ ተግባራት ላይ መሰማራት አይችልም። በሌላ መልኩ በአንቀፅ 2(3፣4፣19 እና 12) ስር የተካተቱት ማለትም የቶምቦላ ወይም ራፍል ሎተሪ፣ የስፖርት ውርርድ ሎተሪ፣ ኮንቬንሽናል ቢንጎና የፕሮሞሽን ሎተሪ በማንኛውም ሰው ሊሰሩ የሚችሉ ናቸው። ከዚህ ሌላ በተለይ የቶቶና ፈጣን ሎተሪዎችን አስተዳደሩ አስፈላጊው ካፒታል፣ ቴክኖሎጂና የእውቀት አመራር ያላቸው የግል ተሳታፊዎች ጋር በጋራ ሽርክና ሊሰራቸው የሚችሉ ስለመሆናቸው ተመላክቷል።
ከዚህ ባለፈ ደንቡ በአንቀፅ 17 ስር ውስን ክልከላዎችን ያስቀመጠ ሲሆን በዚህም፣- ማንኛውም ሰው ከአስተዳደሩ የተሰጠ ፈቃድ ሳይኖረው ማንኛውንም የሎተሪ ሥራ ማካሄድ አይቻልም፣ በተጨማሪም ማንኛውም ሰው የሎተሪ ሥራ ለማካሄድ የተሰጠውን ፈቃድ ያለአስተዳደሩ ስምምነት ለሌላ ሰው አሳልፎ መስጠት
የተከለከለ ተግባር መሆኑ ተደንግጓል።
ክልከላዎችን መተላለፍና የወንጀል ተጠያቂነት
በደንቡ አንቀፅ 20 ስር ግልፅ የወንጀል ክልከላዎች የተቀመጡ ሲሆን በዚህም በወንጀል ህጉ ከፍ ያለ ቅጣት ከሌለ በቀር ማንኛውም ሰው የፀና ፈቃድ ሳይኖረው የሎተሪ ስራ ያካሄደ እንደሆነ ከሃምሳ እስከ መቶ ሽህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እና ከሦስት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት ይቀጣል። እንዲሁም ማንም ሰው የህንፃ ይዞታውን ለህገ-ወጥ የሎተሪ መሸጫ እንዲውል ያከራየ ወይም በማንኛውም ሁኔታ የተፈቀደ ወይም በአስተዳደሩ ለቁጥጥር የተላከን ሰራተኛ እንዳይገባ የከለከለ ወይም የቁጥጥር ሥራው እንዳይካሄድ በማንኛውም መንገድ ያሰናከለ ከብር አስር ሺህ እስከ ሃያ ሺህ ብር መቀጮ እና ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ የእስር ቅጣት ይቀጣል።
ከእነዚህ በዝርዝር ከሰፈሩት የሚያስቀጡ ተግባራት በተጨማሪ እንደተፈፀመው ድርጊት ሁኔታ የወንጀል ህጉ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ተፈፃሚ ይሆናሉ። በዚህም ምሳሌ በአንቀፅ 692 ስር አታላይነትን አስመልክቶ የሚከተለው ሰፍሯል፣-
ማንም ሰው የማይገባ ብልፅግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ አሳሳች የሆኑ ነገሮችን በመናገር የራሱን ማንነት ወይም ሁኔታ በመሰወር፣ ወይም መግለፅ የሚገባውን ነገር በመደበቅ ወይም የሌላውን ሰው የተሳሳተ እምነት ወይም ግምት በመጠቀም ፣ በማድረግ ሆነ ባለማድረግ ሌላውን ሰው አታሎ የራሱን ወይም የሦስተኛ ወገን የንብረት ጥቅም የሚጎዳ አድራጎት እንዲፈፀም ያደረገ እንደሆነ በቀላል እስራት ወይም እንደነገሩ ከባድነት ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና በመቀጮ እንደሚቀጣ ተደንግጓል።
በመጨረሻም ምንም እንኳ በዚህ ፅሁፍ የተሸፈነውን አዋጅ ቁጥር 535/1999 በግልፅ ባይሽረውም በ2001 ዓ.ም በይዘት ከአዋጁ ብዙም ያልተለየ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደርን ለማቋቋም የወጣ ደንብ ቁጥር 160/2001 በሥራ ላይ ይገኛል። ደንቡ በአዋጁ ከተካተቱት የወንጀል ቅጣቶች በተጨማሪ ዝርዝር አስተዳደራዊ ቅጣቶችን ያካተተ ሲሆን በተለይም በሐሰተኛና በተጭበረበረ ማስረጃ የተገኘ ፈቃድ ሲሆን፣ ፈቃዱ የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ወይም የሀገሪቱን ደህንነት የሚጎዳ የወንጀል ተግባር ሲሰራበት፣ በተሰጠው የጊዜ ገደብ (በየበጀት አመቱ) ያላሳደሰ እንደሆነ እንደሁኔታው ከማገድ እስከ ፈቃድ ስረዛ የሚደርስ እርምጃ ለመውሰድ ይችላል።
ማጠቃለያ
የሎተሪ ጨዋታ ራሱን የቻለ በእድል ጨዋታ የተመሰረተ የስራ ዘርፍ (Gaming Profession) ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ሥራ ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች አሁን በስራ ላይ ባለው የንግድ ህግ በተለይም አንቀፅ 5 ስር እንደተመላከተው ነጋዴ ሊባሉ የሚችሉ ስላልሆኑ የንግድ ፈቃድ ምዝገባ ማድረግ አይጠበቅባቸውም። በአንፃሩ ከፍ ብሎ እንደተብራራው በሎተሪ ሥራ ውስጥ የሚሰማራ ማንኛውም ሰው ግንኙነቱ የሚመራው በደንቡና እሱን ተከትለው በሚወጡ መመሪያዎች መሰረት ሆኖ ግንኙነቱም በዚሁ ደንብ ከተቋቋመው የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ጋር ይሆናል።
ሌላው በዚህ ፅሁፍ ሽፋን የተሰጠው የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደርን እንደገና ለማቋቋም የወጣው ደንብ ቁጥር 160/2001 ሲሆን ነገር ግን ደንቡ በተለይ በአንቀፅ 20 ላይ የደነገጋቸው የወንጀል ቅጣቶች ከደንቡ በፊት በሥራ ላይ ከነበረው አዋጅ 535/1999 በቀጥታ የመጡ እንደሆኑና በኢፌዲሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 55(5) በሰፈረው መሠረት የወንጀል ህግ የሚወጣው በፌደራሉ የህግ አውጭ ምክር ቤት ብቻ በመሆኑ የወንጀል ቅጣት የያዘው የአዋጁ ድንጋጌ ያልተሻረ ስለመሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል።
በንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ
የፍትሕ ሚኒስቴርን የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆችን እና ድረ-ገጽን ይቀላቀሉ
Website
https://www.justice.gov.et
Facebook
https://www.facebook.com/MOJEthiopia/
(x) Twitter
https://x.com/MOJEthiopia
YouTube channel
https://youtube.com/...3701 ...
LinkedIn
https://www.linkedin.com/.../ministry-of-justice.../about/
Telegram
https://t.me/fdreattorneyGeneral_externa