03/06/2026
የም/ቤቱ 23ኛ መደበኛ ስብሰባ ነገ ይካሄዳል
------------------
(ዜና ፓርላማ) ግንቦት 26፣2018 ዓ.ም፤ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ 23ኛ መደበኛ ስብሰባውን ነገ ግንቦት 27 ቀን፣ 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
ም/ቤቱ በነገ ስብሰባው በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ልማት ባንክ ፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በዓለምዓቀፍ የልማት ማህበር መካከል የተደረጉ የብድር ስምምነቶች ለማፅደቅ የወጡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግሥትና እና በሴራሊዮን ሪፐብሊክ መንግሥታት፤ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግሥት እና በአንጎላ ሪፐብሊክ መንግሥታት፤ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግሥት እና በባንግላዲሽ ሕዝባዊ ረፐብሊክ መንግሥታት፤ እንዲሁም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግሥት እና በኢስዋቲኒ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት
መካከል የተፈረመውን የሁለትዮሽ የአየር አገልግሎት ስምምነት ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀረበውን ሪፖርትና ውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን የሚያፀድቅ ይሆናል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግሥት እና በሩሲያ ፌዴሬሽን መካከል የጋራ የባዮሎጂ ምርምር ማዕከል ለማቋቋም የተፈረመውን ስምምነት ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀረበውን ሪፖርትና ውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል።
በተያያዘም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግሥት እና በቬትናም ሶሻሊስት ሪፐብሊክ መንግሥት መካከል የዲፕሎማቲክ ወይም ኦፊሻል የአገልግሎት ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን ለማስቀረት የተፈረመ ስምምነት ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀረበውን ሪፖርትና ውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን ያፀድቃል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን፣ የግብርና ቢዝነስ ኩባንያ ረቂቅ አዋጅን፣ የምግብ ስርዓትና ስርዓተ ምግብ ረቂቅ አዋጅን ፣ የኢትዮጵያ የካርበን ገበያ ረቂቅ አዋጅን እና የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ይመራል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament
በዩቲዩብ
https://www.youtube.com/
በቴሌግራም
https://t.me/ParlamaNews
በትዊተር
http://twitter.com/fdrehopr
በዌብሳይት
www.hopr.gov.et ይከታተሉ።