28/05/2026
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ከሚዲያዎች ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን የሚዲያ ፎረም አካሄደ
ግንቦት 20 ቀን 2018 (ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል አዲስ አበባ)፡- የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ተደራሽነቱን ይበልጥ ለማሳደግ ይረዳው ዘንድ በዛሬው ዕለቱ የተለያዩ የሚዲያ ባለሙያዎችን ጠርቶ የሚዲያ ፎረም አካሂዷል፡፡
የሆስፒታሉ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር መገርሳ ዓለሙ፣ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ረድዔት ሰለሞን እንዲሁም የአዕምሮ ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ አስከ አሁን ያለውን አጠቃላይ ሂደት በተመለከተ ለጋዜጠኞች ገለጻ አቅርበዋል፡፡
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በተለየ ሁኔታ የሚታወሰው በኮቪድ ወቅት በማገገሚያ ማዕከልነት በማገልገል ባበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲሆን ሆስፒታሉ ከዚያም በተጨማሪ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረው ግጭት ሳቢያ በተወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ የጦር ጉዳተኞችን ተቀብሎ የህክምና እርዳታ ሲያደርግ መቆየቱንም ዶ/ር መገርሳ አንስተዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም በወቅቱ አገልግሎት ሲሰጡ ለነበሩ ክፍሎች የእድሳት ስራ ማካሄድና የአገልግሎት ጥራቱን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ወደ እድሳት ተገብቶ የሱስ ማገገሚያ ተኝቶ ህክምናን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ አገልግሎቶችን በማካተት እድሳቱ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ከ90 በላይ ሰብ ስፔሻሊስቶች ያሉትና በሰው ኃይልም ሆነ በመሳሪያ ዘመኑ በሚፈልገው ደረጃ የታጠቀና እንደ አገር የሜዲካል ቱሪዝም አገልግሎት እውን ለማድረግ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ከድጅታላይዜሽንም አንጻር ሆስፒታሉ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ከወረቀት ነጻ ለማድረግ መሰረተ ልማቶችን የሟሟላት ስራ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝና የቅሬታ አቀራረብ ስርዓትም ድጅታል ሆኖ በጽሁፍ፣ በድምጽ እና በፎቶ አስደግፎ ማቅረብ የሚቻልበት ስርዓት መዘርጋቱን አንስተዋል፡፡
ሆስፒታሉ ወደ ተቋሙ የሚመጡትን ብቻ ሳይሆን እንደ ሜቄዶንያ፣ ዲቦራ ፋውንዴሽን፣ ቦርን አጌይን በሚባሉ ድርጅቶችና በአካባቢው ያሉ ትምህርት ቤቶች ድረስ በመሄድ ነጻ የህክምናና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የትምህርት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ዶ/ር ረድኤት ሰለሞን ተናግረዋል፡፡ የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የአእምሮና የአካላዊ ህክምናን አጣምሮ የያዘ ከመሆኑም በተጨማሪ የሆስፒታሉ ስፋትና ወጣ ብሎ የሚገኝ መሆን ለአእምሮ ህመም ታካሚዎች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑ ከሌሎች ሆስፒታሎች ልዩ ያደርገዋል ሲሉ ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሚዲያ ባለሙያዎችም የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተው በበላይ ኃላፊዎቹ ምላሽና ማብራሪያዎች የተሰጡ ሲሆን የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ከሌሎች ሆስፒታሎች በተለየ የአእምሮና የአካላዊ ህክምናን አጣምሮ መያዙ የታካሚዎችን እንግልትን የሚቀንስና የአእምሮ ህመም ታክሞ መዳን ምጣኔን የሚያሳድግ በመሆኑ የሚበረታታ ተግባር እንደሆነ ተሳታፊዎቹ ጨምረው አንስተዋል፡፡
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በምስራቅ አፍሪክ ብቸኛ የስነ አዕምሮ ህክምና ማዕከል የመሆን ርዕዩን እውን ለማድረግም በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ የካበተ ልምድ ካላቸው ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነቶችን በመፈራረምና ትስስሮችን በማጠናከር እየሰራ እንደሚገኝ ዶ/ር መገርሳ ዓለሙ ተናግረዋል፡፡
በፎረሙ ላይ የተሳተፉ የሚዲያ ባለሙያዎች በሆስፒታሉ ኢክስኪዩቲቭ ዳይሬከተር አስጎብኚነት የሆስፒታሉን አገልግሎት መስጫ ክፍሎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
“የአገልግሎት ጥራት አርማችን!”