18/02/2025
በሽግግር ፍትህ ትግበራ ሂደት ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተከናወኑ ተግባራት እንደሚከተለው ቀርበዋል
1. የሽግግር ፍትህ ረቂቅ የህግ ማዕቀፎችን በመድብል መልክ የማጠቃለል ስራው ተጠናቋል፡፡ በዚህም መሰረት የባለሙያዎች ቡድኑ የሽግግር ፍትህ ልዩ ችሎት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን እና የአለም አቀፍ ወንጀል ህግ አዋጅን እራሳቸውን ችለው እንዲቀጥሉ ያደረገ ሲሆን የሽግግር ፍትህ ተቋማትን ማለትም የልዩ ዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤትን፣ የእውንት ኮሚሽንን እና የማጥራት ኮሚሽንን የሚያቋቁሙ ድንጋጌችን በመጽሃፍ በመከፋፈል በመድብል መልክ የማዘጋጀት ስራውን አጠናቋል፡፡ በቀጣይ ቀናትም የባለሙያዎች ቡድኑ በህግ ረቂቆች ላይ የሚያደርገውን የመጨረሻ ውይይት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
2. በሽግግር ፍትህ ሂደት ባለቤት ከሆኑት የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል ሁለቱ ተጎጂዎች እና ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ በፍኖተ ካርታው ላይ በሰፈረው መሰረትም የእነኚህን ተሳትፎ በሂደቱ ለማረጋገጥ የሚያስችል ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ውይይቱን መሰረት አድርጎ የተነሱ ሃሳቦችን በማካተት በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጨረሻው የስትራቴጂ ሰነድ ለህዝብ የሚጋራ ይሆናል፡፡ በዚህ ሰነድ ሴቶች፣ ህጻናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ ተፈናቃዮች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን እና በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጉዳት የደረሰባቸው ተጎጂዎች በሁሉም የሽግግር ፍትህ ማስተግበሪያ ስልቶች አተገባር ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያበረቱቱ መርሆዎች እና አሰራሮችን የሚመለከቱ ሃሳቦች ተካትተዋል፡፡
3. የሽግግር ፍትህ ረቂቅ ህጎች የግብዓት ማሰባሰቢያ የምክክር መድረኮች የመመሪያ ማእቀፍ እና የድርጊት መርሃ ግብር ረቂቅ ተጠናቆ ለአስተያየት ለባለሙያዎች የተሰራጨ ሲሆን በግብዓቶቹ መሰረት ሰነዱን በማጠናቀቅ በቀጣይ ለሚካሄደው ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ ጥቅም ላይ እንዲውል በጥንቃቄ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ ሰነድ ውስጥ በምክክር መድረኩ የሚሳተፉ ሰዎች፣ ውይይቶቹ ስለሚካሄዱባቸው ቦታዎች፣ ተሳታፊዎች ስለሚለዩበት ሁኔታ እና በመለየት ሂደቱ ሊሳተፍ ስለሚገባ አካላት፣ የጊዜ እና የበጀት መግለጫዎች ተካተዋል፡፡
4. በሽግግር ፍትህ ሂደት ለትምህርት የሚሆን ልምድ ካላት ሀገር ኮሎምቢያ አምባሳደር የተከበሩ YEISON ARCADIO MENESES COPETE ጋር የሽግግር ፍትህን አተገባበር ውጤታማነት ለማስጠበቅ የኮሎምቢያ ኤምባሲ ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት ለመስራት ፍላጎቱን የገለጸበት የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡ በዚህ በፍትህ ሚኒስቴር በተካሄደ የውይይት መድረክ የኮሎምቢያ አምባሳደር ሀገራቸው ለኢትዮጵያም ሆነ ለሌሎች በተመሳሳይ ሂደት ውስጥ ለሚገኙ ሀገራት ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ እንደሆነች ገልጸው ሀገራቸው በኢትዮጵያ የተጀመረው የሽግግር ፍትህ እውን እንዲሆን እስከ መጨረሻው ድጋፏን እንደምትቀጥል ገልጸዋል፡፡
5. የሽግግር ፍትህን ሂደት አስመልክቶ ለፍትህ ሚኒስቴር እና ለክልል ፍትህ ቢሮዎች አመራሮች ገለጻ ቀረበ፡፡ የፍትህ ሚኒስቴር እና የክልል ፍትህ ቢሮዎች፣ የፌዴራል እና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች፣ የፍትህ ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት አመራሮች በተገኙበት በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በተካሄደው 7ኛው የጋራ ጉባዔ ላይ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሂደትን የሚመለከት ገለጻ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡