03/06/2026
#7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ አፈፃፀም በዳሰነች ወረዳ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተገመገመ
ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ/ም ኦሞራቴ፣ በዳሰነች ወረዳ በታሪካዊነቱና በከፍተኛ ህዝባዊ ተሳትፎው የሚታወሰው 7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ አጠቃላይ አፈፃፀምን አስመልክቶ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰፊ የግምገማና የውይይት መድረክ አካሄደ።
በግምገማ መድረኩ ላይ እንደተገለጸው በወረዳው የተካሄደው ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የጋራ ምክር ቤቱና መላው የወረዳው ማህበረሰብ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
በወረዳው በአጠቃላይ 43,679 ዜጎች በነቂስ ወጥተው ድምጽ በመስጠት ሉዓላዊ መብታቸውን ተጠቅመዋል። ይህ ቁጥር በወረዳው የፖለቲካ ንቅናቄና በምርጫ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ የተመዘገበበት መሆኑ የዳሰነች ወረዳ ረዳት የመንግሥት ተጠሪ እና የፖለቲካና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሣዳም አሊ ተናግረዋል። በምርጫው ሂደት ላይ የሴቶች ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ ጎልቶ የታየበትና በድምጽ አሰጣጡም ላይ ያሳዩት ተደራሽነት አመርቂ እንደነበር ተጠቁሟል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤቱ አማካኝነት የነበሩትን ልዩነቶች በውይይት እየፈቱ ለህዝብ ሰላምና ለምርጫው ስኬት በቅንጅት መስራታቸው ለሌሎች አካባቢዎች አርአያ የሚሆን ተግባር መሆኑ የጋራ ም/ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ እና የዳሰነች ወረዳ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ሪኮይ አሪከር ተናግረዋል።
"ይህ 7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በዳሰነች ወረዳ በሰላም መጠናቀቁ የህዝባችንን የዴሞክራሲ ባህል ማደግ የሚያሳይ ሲሆን ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤት ደረጃ ያሳዩት የመደማመጥና አብሮ የመስራት መንፈስ የወረዳችንን ልማትና አንድነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው" ሲሉ የጋራ ም/ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ገልጸዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ታዲዮስ ለበን በበኩላቸው ከምርጫው ሂደት የተገኙ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠልና በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የታዩ ውስንነቶችን በማረም በቀጣይም በወረዳው ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የህዝብን አንድነት ለመገንባትና የአካባቢውን ልማት ለማፋጠን በጋራና በትብብር መንፈስ እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ታዲዮስ ለበን በቅርቡ የተካሄደውን የምርጫ ውጤት በሙሉ ልብ እና በፀጋ እንደሚቀበሉ የገለጹ ሲሆን የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምን ትልቁ አሸናፊ የኢትዮጵያ ሕዝብና የጀመርነው የዲሞክራሲ ሥርዓት ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ምርጫው የሕዝብን ድምፅና ፍላጎት ያንጸባረቀ በመሆኑ ሂደቱን ማክበርና ውጤቱን በየዋህነትና በዲሞክራሲያዊ መንፈስ መቀበል የሁሉም ወገን ኃላፊነት መሆን አለበት ብለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ አመራሮች በሰጡት መግለጫ ምርጫው በስኬት መጠናቀቁ የወረዳው ህዝብ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ነው ብለዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤቱ በኩል ያሳዩት የጎለበተ የፖለቲካ ባህል፣ መቻቻል እና ለህዝብ ሰላምና አንድነት ቅድሚያ የመስጠት መርህ ለሌሎች አካባቢዎች አርአያ መሆን የሚችል መሆኑም ተመላክቷል።
"ይህ ምርጫ የዳሰነች ወረዳ ህዝብ የዴሞክራሲ ብስለቱንና የሰላም ወዳድነቱን በተግባር ያረጋገጠበት ታሪካዊ መድረክ እንደሆነ ሀሳባቸውን ገልፀዋል።
ምክር ቤቱ የግምገማ መድረኩን ሲያጠቃልል ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የልማት ስራዎችን ማጠናከር እንዳለበትና ህዝቡ በምርጫው ያሳየውን ከፍተኛ ተነሳሽነት ወደ ልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች በመቀየር የወረዳውን ሁለንተናዊ እድገት ማፋጠን እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በተጨማሪም አብሮነትን ማጠናከርና ከምርጫው ማጠናቀቅ በኋላም ቢሆን በፓርቲዎችና በማህበረሰቡ መካከል ያለውን የጋራ ተጠቃሚነትና የሰላም እሴት ይበልጥ ማጎልበት እንደሚገባ ተገልጿል።
በመጨረሻም፣ ምክር ቤቱ ለምርጫው ስኬታማነት ሌሊትና ቀን ለደከሙ የፀጥታ አካላት፣ ለምርጫ አስፈፃሚዎች እና ሙሉ ሂደቱን በሰላማዊ መንገድ ላጠናቀቀው መላው የዳሰነች ወረዳ ህዝብ ላቅ ያለ ምስጋና አቅርቧል።
።