31/03/2026
መንግሥት በነዳጅ አቅርቦት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመቋቋም የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ይፋ አደረገ
*****
በመካከለኛው ምስራቅ ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ ወደሃገር ውስጥ መግባት የነበረበት ከ180,000 ሜትሪክ ቶን በላይ ነዳጅ በወቅቱ መድረስ ባለመቻሉ፣ የፌደራል መንግሥት ሰፊ የነዳጅ አቅርቦት ቅድሚያ መስጫ እርምጃዎችን ያስተዋወቀ ሲሆን በህገ-ወጥ ንግድ ላይ የሚደረገውን ቁጥጥርም አጠናክሯል።
በዚህም፣ በመካካለኛው ምስራቅ ያለው ጦርነትና አለመረጋጋት በሀገራችን የነዳጅ ግብይትና አቅርቦት ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተጽዕኖ እንዲሁም መንግሥት የሚከተላቸውን አቅጣጫዎች በተመለከተ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫውም፣ የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭትን የሚከታተል፣ ርምጃ የሚወስድና የነዳጅ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ዘርፎች የሚለይ ልዩ ክፍል መቋቋሙ ይፋ ተደርጓል።
በጦርነቱ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጦርነቱ በፊት የአንድ በርሜል ነጭ ናፍጣ ዋጋ 80 ዶላር የነበረ ሲሆን:- አሁን 230 ዶላር መድረሱን፣ ቤንዚንም ከ70 ወደ 150 ዶላር ማሻቀቡ ተጠቁሟል።
በነጭ ናፍጣ ላይ የነበረው የቀን አቅርቦት ከ9 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሊትር ወደ 4 ነጥብብ 5 ሚሊዮን ሊትር ዝቅ ሊል ችሏል።
መንግሥት የተፈጠረውን የአቅርቦት እጥረት ለመቅረፍና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዳይገቱ ነዳጅን ከተጓዳኝ ገበያ ስለሚገዛና የዓለም የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት በሦስት እጥፍ ዋጋ እየገዛ በማቅረብ ላይ ይገኛል።
ምንም እንኳን የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ቢጨምርም መንግሥት የዜጎችን ኑሮ ለመታደግ በአሁኑ ወቅት በነጭ ናፍጣ ላይ በአንድ ሊትር 95 ብር በቤንዚን ላይ ደግሞ 42 ብር ድጎማ እያደረገ ይገኛል።
መንግስት እስካሁን 262 ቢሊዮን ብር ገደማ ድጎማ ማድረጉን እና በየወሩም ከ15 እስከ 20 ቢሊዮን ብር ለድጎማ እየተመደበ መሆኑም ተጠቅሷል።
በመሆኑም ያጋጠመው የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በሀገርና በዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እንዳያሳድርና በፍትሐዊነት ለመምራት መንግሥት ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የቅድሚያ አሰጣጥ ውሳኔ አሳልፏል።
በዚህም መሠረት
1. ነዳጅ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች በማደያ የቅድሚያ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው፣
2. ከፍተኛ አምራችና የኤክስፖርት ድርጅቶች በቀጥታ፣
3. ልዩ ትኩረት የሚሹ የመንግሥትና የግል ፕሮጀክቶች በቀጥታ፣
4. የገቢና ወጪ ንግድን ጨምሮ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች
5. ግብርናን የሚያዘምኑ ትራክተሮች፣
6. የከተማና ሀገር አቀፍ የብዙሃን ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች
7. እንዲሁም በናፍጣ የሚሰሩ ሌሎች ለህብረተሰብ ግልጋሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች በቅድሚያ እንዲያገኙ የሚያደርግ የቅድሚያ የነዳጅ አጠቃቀም አሠራር የሚተገበር መሆኑ ተገልጿል።
በመግለጫው ከሕብረተሰቡ የሚከጠበቁ ተግባራትን ይፋ የተደረጉ ሲሆን በዚህም መሠረት፦
1) ነዳጅን በቁጠባ እንዲጠቀም፣
2) የታዳሽ ኃይል አማራጮችን የመጠቀም ስልትን መከተል፣
3) የእግር ጉዞ ባህልን ማጎልበት
4) አላስፈላጊ የጉዞ ፕሮግራሞችን መሰረዝና ማቆም
5) የሕዝብ ትራንስፖርትን መጠቀም
6) በነዳጅ ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ተግባራትን በማጋለጥ ረገድ ከመንግሥት ጋር ተባብሮ እንዲሠራ ጥሪ ተደርጓል።
በመሆኑም በሃገራችን የሚገኙ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ይህን ግዜ ከህዝብ ጎን በመሆን በፅናት ለማለፍ እና እንደሃገር የወጣውን መመሪያ በማክበር መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
በተጨማሪም፣ ያለውን የነዳጅ አቅርቦት በቁጠባ በመጠቀም እና ተያያዥ የኑሮ ውድነት እንዳይከሰት፣ ብሎም ያጋጠመው የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በሀገርና በዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመቀነስ በትኩረት በመስራት እንደሁልጊዜው የህዝብ አጋርነታቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡
መረጃውን ከኢዜአ ወስደናል