04/06/2026
7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የተምሳሌት ጉዞ ማሳያ!
ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ታሪኳ ውስጥ አዲስና ብሩህ ምዕራፍ የከፈተችበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው። ይህ ምርጫ ተራ የድምፅ መስጠት ሂደት ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በነፃነት፣ በሰላምና በብስለት የራሱን ዕድል በራሱ መወሰን እንደሚችል ለዓለም ያስመሰከረበት ታላቅ ሁነት ነው።
ምርጫው ኢትዮጵያ ማንኛውንም የውስጥ እና የውጭ ፈተናዎች እየተሻገረች ወደ ከፍታ የምታደርገው ግስጋሴ ለአፍታም እንደማይገታ ዳግም ያረጋገጠችበት ሲሆን፤ ለሀገራችን ሉዓላዊነት ተጠብቆ መዝለቅ የተጣሉ ፅኑ መሰረቶችን ጥንካሬም ማሳየት ችሏል፡፡
ይህ ታሪካዊ ምርጫ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በአጠቃላይ በአህጉሩ የእውነተኛ ዴሞክራሲ ተምሳሌት ለመሆን የምታደርገውን ጉዞ በተግባር ያበሰረ ነው። የምርጫው ሂደት በሰላማዊ መንገድ መከናወኑ፣ የዜጎች በነፃነት የመሳተፍ መብት መረጋገጡ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰለጠነ እና ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ሃሳባቸውን የሚያቀርቡበት አውድ መፈጠሩ የፖለቲካ ባህል ግንባታ ጉዞአችንን ከፍ አድርጎታል።
ኢትዮጵያውያን የሀሳብ ልዩነቶቻቸውን በግጭት እና በጦርነት ሳይሆን በንግግር፣ በውይይትና በህዝባዊ ውሳኔ መፍታት የሚችሉባቸው እሴቶች እንዳሏቸው ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳየት በኩልም 7 ኛው ሀገራዊ ምርጫ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡