03/02/2022
35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ባለሁለት እግር ሞተር ብስክሌት ማሽከርከር የተከለከለ መሆኑን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ- ኃይል አስታወቀ፡፡
***
35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ጥር 28 እና 29 ቀን 2014 ዓ/ም ይካሄዳል፡፡ ጉባኤው በሰላም እንዲጠናቀቅ ለማስቻል ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ወደ ስራ መግባታቸው ይታወቃል፡፡ ህብረተሰቡም ለጉባኤው ስኬታማነት የድርሻውን እንዲወጣ የቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ አካባቢውን እየጠበቀ ይገኛል፡፡
የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ- ኃይል ከአዲስ አበባ ከተማ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ጋር በጋራ በተወሰነው መሰረት አሁን ያለውን የፀጥታ ሁኔታ በተገቢው ለመምራትና ለእንግዶቹ አስፈላጊውን አቀባበል ለማድረግ እንዲሁም የትራፊክ ፍሰቱን የተሳለጠ ለማድረግ ከነገ አርብ ጥር 27 ቀን 2014 ዓ/ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት የፀጥታ አካላት ከሚጠቀሙባቸው ውጪ ባለሁለት እግር ሞተር ብስክሌት በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም አከባቢዎች በማንኛውም ሰዓት መንቀሳቀስ ፍፁም የተከለከለ መሆኑን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ- ኃይል አስታውቋል፡፡
የሞተር ብስክሌት ባለንብረቶች ሆኑ አሽከርካሪዎች ይህንን መልእክት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ግብረ ኃይሉ መልእክቱን እያስተለለፈ ይህንን መልእክት በሚተላለፉ አካላት ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡