18/12/2023
ልጆች ከፍ ያለ ግምት እንደተሰጣቸው እንዲሰማቸው ከአዋቂዎች የሚፈልጓቸው 6 ነገሮች
ክፍል አንድ
👫ልጆች በጣም አስደሳች ፍጡራን ናቸው! ነገርግን ዓለምን የሚገነዘቡት መንገድ ከአዋቂዎች የተለዬ ነው፡፡ ከአካባቢያቸውም የሚጠብቁት ነገር አዋቂዎች ከሚጠብቁት ከተለመደው ነገር በጣም ከፍ ያለ ነው፡፡
📌በዚህ ትልቅ ዓለም ውስጥ ስለራሳቸው ያላቸው ግንዛቤ ለብዙ ጥሩም ሆነ መጥፎ ስሜቶች እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል።
📌ልጆች በዚህ የልጅነት እድሜ ክልላቸው ስብዕናቸውን፣ ችሎታቸውን እና ለራሳቸው ያላቸውን ግምት ሙሉ በሙሉ አዳብረው ስላልጨረሱ፣ በዙሪያቸው ያሉ አዋቂዎች በራስ የመተማመን ስሜታቸውን ለማሳደግ በንቃት ክትትልም፤ ጥረትም ማድረግ አለባቸው። እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ልጆች ከፍ ያለ ግምት እና ክብር ይሰማቸዋል ወይም ስሜቱን መረዳት ይጀምራሉ፡፡
📌ልጆች በዙሪያቸው በሚገኙ ለነሱ ትርጉም ባለቸው አዋቂዎች እንደተወደዱ፣ እንደተደመጡ እና እንደሚከበሩ ሲሰማቸው በእነዚህ ምላሾች ላይ በመመስረት ማንነታቸውን ያዳብራሉ። አብዛኛዎቹ ልጆች ከአዋቂዎች ብዙ ነገር አይፈልጉም፤ በአንጻሩ በቀላሉ በዙሪያቸው እና በሚወዷቸው ሰዎች ህይወት ውስጥ ቦታ እንዲኖራቸው ብቻ ነው የሚፈልጉት፡፡
📌ልጆች ጤናማ ማንነት እና በራስ የመተማመን ደረጃ እንዲመሰርቱ ለመርዳት በሕይወታቸው ውስጥ ያሉ ለነሱ ትርጉም ያላቸው አዋቂዎች ያስፈልጓቸዋል። በዚህ የልጆች የስሜታዊ እድገት ዙሪያ ልጅዎን ለመርዳት የሚከተሉት 6 መንገዶች ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።
✅1. ጓደኝነት መፍጠር፡ ይህ በጣም ቀጥተኛ ምክር ነው፣ ግን በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ብዙ ወላጆች ከልጃቸው ጋር ሊኖራቸው የሚገባውን ከትስስር መፍጠሪያ መንገዶች አንዱ የሆነውን የጓደኝነት ግንኙነት ችላ ይሉታል። ከልጅዎ ጋር የሚያሳልፉት የብቻዎ ጊዜ፣ መከባበርን፣ መቀራረብን እና ግንኙነትን ለመገንባት በጣም አስፈላጊ ነው። በውጤቱም ልጅዎ እርስዎን በሚፈልጉበት ጊዜ ወደ እርስዎ ለመምጣት ምቾት እንዲሰማው ያደርገዋል፡፡
✅2. ፍቅርን መግለጽ፡ ልጆች በሕይወታቸው ውስጥ ባሉ አዋቂዎች እንደሚወደዱ ማወቅ በእጅጉ ይፈልጋሉ። በቤተሰቦቻቸው መካከል ያለው ትዳር ወይም ግንኙነት ከአሁን በኋላ ሊሠራ የሚችል ባይሆንም እንኳን በዛ ትዳር/ግንኙነት ውስጥ የተፈጠሩ ልጆች አሁንም በሁለቱም ወላጆች እንደሚወደዱ እና እንደሚደግፉ እርግጠኛ መሆን ይፈልጋሉ፡፡ ማረጋገጥም አለባቸው፡፡ ልጆችዎ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንደምትወዷቸው ማወቅ አለባቸው። ለምሳሌ ወንድ ልጅዎ ጥሩ የእግር ኳስ ተጫዋች ላይሆን ይችላል፤ እንደውም ከነአካቴው ኳስ ላይወድ ይችላል፡፡ ነገር ግን እሱ በራሱ የራሱ ፍላጎቶችና ችሎታዎች ያሉት የተለየ ሰው እንደሆነ መገንዘብ አለብን፡፡ ስለዚህ ልጆችን በሚያደርጉት ነገር ሳንፈርድ እና ቅድመ ሁኔታ ሳናስቀምጥ ዝም ብለን አዎንታዊ ድጋፍ ልናደርግላቸው ይገባል፡፡
✅3. ውይይት ማድረግ፡ ይህ ሲታይ ቀላል ነገር ሊመስል ይችላል ነገርግን አዋቂዎች ብዙውን ጊዜ ልጆች ከእነሱ ጋር መነጋገር እንደማይወዱ ነው የሚያስቡት። ይህ እውነት አይደለም፡፡ ብዙ ልጆች ከአዋቂዎች ጋር ማውራት ያስደስታቸዋል ምክንያቱም የብስለት ወይም የአዋቂነት ስሜት ስለሚሰጣቸው ነው። በዓለማችን ላይ እየተፈጠሩ ስላሉ ክስተቶች፣ ስፖርታዊ ክንውኖች፣ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች፣ ፍላጎቶች፣ በትምህርት ቤት ውስጥ ስለተከሰቱት ነገሮች ወዘተ ማውራት ልጅዎ ምክር ወይም እርዳታ ከፈለጉ ወደ እርስዎ ለመምጣት ቀላል እንዲሆንላቸው በር ይከፍታል፡፡ ስለዚህ ልጆችዎ ጋር ምቹ ሁኔታዎችን ከግምት ያስገባና የተመጠነ ጊዜን ያማከለ ውይይት ያድርጉ፡፡
✅4. ድንበሮችን ማስቀመጥ:- ምንም እንኳን ከልጆችዎ ጋር ጓደኝነት መፍጠር እንዲሁም ውይይት ማድረግ አስፈላጊ ነገሮች ቢሆኑም ልጆቻችሁ በቤተሰቡ ውስጥ አዋቂ ሰው እናንተ እንደሆናችሁ እንዲያውቁ ትፈልጋላችሁ። ልጆቻችሁ “በእርስዎ ደረጃ ላይ” እንደሆኑ እንዲሰማቸው በጭራሽ አትፈልጉም። ይህ አስቸጋሪው የወላጅነት ክፍል ነው፡፡ ልጅዎ ደህንነት እንዲሰማው በቤት ውስጥ ስርዓትንና ቁጥጥርን ማስፈን ይፈልጋሉ ነገር ግን ደግሞ እንደ ልዩ ሰው ለልጆችዎ ከበሬታን በማሳየትና ለነሱ ተገቢውን ዋጋ እንዲሰማቸው በማድረግ እነሱን መርዳት ይፈልጋሉ። ይህንን ሚዛን በትክክል ለማስጠበቅ የልጅዎን ስብዕናና የማንነት ደረጃ ግምት ውስጥ ማስገባት አለብዎት፡፡ አንዳንድ ልጆች ጥብቅ መመሪያ እና ድንበሮች ሲያስፈልጋቸው ሌሎች ልጆች ደግሞ በበለጠ ነፃነት ውስጥ መልካም እድገት ያሳያሉ፡፡ ስለዚህ የትኛው ልጅዎ ላይ የትኛው መንገድ ውጤታም እንደሚሆን መምረጥ የርስዎ ፋንታ ነው፡፡ ያኔ ልጆችዎም የሚፈልጉት ከፍያለ ግምት እንደተሰጣቸው የመሰማት ነገር ይመጣል ማለት ነው፡፡
✅5. አክብሮት ማሳየት:- ብዙ ወላጆች ለልጆቻቸው ጸያፍ ቃላትን ባለመናገር ወይም በስድብ ባለመናገራቸው ልጆቻቸውን በአክብሮት እንደያዟቸው ያምናሉ። ይህ በከፊል ትክክል ነው። ነገር ግን ልጆች “አስተዋይ እንደሆኑ” እንዲሰማቸው የእነርሱን አስተያየት ሊያደንቅላቸው በሚችል አዋቂ ሰው መደመጥን ይፈልጋሉ። ከልጆቻችሁ ጋር ስትነጋገሩ እና በተራችሁ ደግሞ እነሱን ስታዳምጡ ሀሳቦቻቸውን እንደምታከብሩላቸው እና ከፍ ያለ ዋጋ እየሰጣችኋቸው እንደሆነ መልዕክት እያስተላለፋችሁ ነው ማለት ነው፡፡
✅6. ወጥ የሆነ ባህሪ ማሳየት፡- ህጻናት ብዙውን ጊዜ አዋቂዎችን የሚመዝኑት ከዚህ ቀደም ባዩት የባህሪ ምልከታ ነው። ስለዚህ ወላጆች እና ሌሎች አዋቂዎች ወጥ/ቋሚ የሆነ ባህሪ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ምንም እንኳን ህፃናት አዋቂዎች ስለአለም ያሏቸውን የተራቀቁ ግንዛቤዎችና ፅንሰ-ሀሳቦች ባይኖራቸውም የልጆችን አስተሳሰብ በቁም ነገር መውሰድ እና እድገታቸውን ያለማቋረጥ በአክብሮት እና በአድናቆት መከታተል ለእነሱ ያላችሁን ከፍተኛ ግምት ያሳያል፡፡
https://www.facebook.com/MSRHChildren
https://t.me/MSRHO
https://www.youtube.com/
https://www.tiktok.com/?_t=8i0YEX0JvM5&_r=1
676 Followers, 1 Following, 185 Likes - Watch awesome short videos created by መልካም ቤተሰብ