09/06/2026
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በበጋ የበጎ ፈቃድ ፕሮግራም የተገነቡ ከ20 በላይ የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ተላለፉ።
በክፍለ ከተማው በሚገኙ ልዩ ልዩ ወረዳዎች በጥቅሉ ከ20 በላይ የሚሆኑ የአቅመ ደካማና አረጋውያን መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ለባለቤቶቻቸው ተረክበዋል።
የቤት ግንባታ ተጠቃሚ የሆኑት ወ/ሮ አሰገደች አሰፋ ከዚህ ቀደም ይኖሩበት የነበረው ቤት በጣም የተጎሳቆለ፣ ለዝናብና ለፀሀይ የተጋለጠ በመሆኑ ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገው እንደነበር ይናገራሉ። ዛሬ ቤታቸው በሚያስደስት ደረጃ ተገንብቶ በመረከባቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ለበጎ ፈቃደኞች ምስጋና አቅርበዋል።
ሌላኛው የቤት ግንባታው ተጠቃሚ አቶ አያሌው ይማም በበኩላቸው፣ ለብዙ ዓመታት ለመኖሪያነት ፍፁም በማይመችና ሙሉ በሙሉ ቆርቆሮ በቆርቆሮ በነበረ ጠባብ ቤት ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ገልጸው፤ "ዛሬ ያ አሰቃቂ ታሪክ ተቀይሮ ቤታችን በብሉኬት ተሰርቶና ዘምኖ በመረከባችን የተሰማንን ደስታ በቃል መግለጽ ይከብዳል" ሲሉ አስተያየታቸውን መስጠታቸውን የላፍቶ ኮሙኒኬሽን ዘገባ ያመለክታል።
የክፍለ ከተማው ህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ብዙአየሁ መኮንን ዛሬ ለተጠቃሚዎች የተላለፉት ቤቶች በበጋ ወቅት በልዩ ትኩረት በእቅድ ተይዘው ሲከናወኑ የቆዩ መሆናቸውን ጠቁመው ፕሮጀክቶቹ ከጅምር እስከ ፍጻሜ ስኬታማ እንዲሆኑ ከጎናቸው ላልተለዩ ቅን ባለሀብቶችና የህብረተሰብ ክፍሎች ምስጋና አቅርበዋል።
በከተማችን ለአቅመ ደካሞች፣ ለአረጋውያን እንዲሁም ለሀገር ባለውለታዎች ደረጃቸውን የጠበቁ መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ከመስጠት ባለፈ፤ የተዛመሙ ጎጆዎችን ባሉበት መልሶ በመገንባት ለኑሮ ምቹ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል።